ወልቂጤ ከተማ በአፍሪካ ታዋቂውን የግብ ዘብ የግሉ አድርጓል

የፊታችን ዕሁድ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት ወልቂጤ ከተማዎች የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂን አስፈርመዋል።

ዘግየት ብለው በዝውውር ገበያው ላይ መሳተፍ የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በዛሬው ዕለት ግብ ጠባቂ ማስፈረማቸው ታውቋል። ለሠራተኞቹ ፊርማውን ያኖረው ተጫዋች ሲላቫይን ጎቦሆ ነው። የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው እና በክለብ ደረጃ ከቲፒ ማዜንቤ ጋር ጥሩ ቆይታ የነበረውን ሲላቫይን ጎቦሆ ከዚህ ቀደም በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ እንደመጣ ይታወቃል። በቅድሚያ 2008 ላይ ቲፒ ማዜንቤ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቶ ሁለት አቻ ሲለያይ የመጣ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ከሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ላይ 2-1 ሲሸነፉ ዓምና መጥቶ ነበር።

በአህጉሩ ከሚታወቁ የግብ ዘቦች አንዱ የሆነው ግቦሆ ሀገሩን በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ ካገለገለ በኋላ ስብስቡን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።