ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አዲስ ረዳት አሰልጣኝ አግኝቷል

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሩዋንዳ ጋር ላለበት ጨዋታ ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አዲስ ረዳት አሰልጣኝ አሳውቋል፡፡

ኮስታሪካ በ2022 ለምታስተናግደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያም ወደዚህ ውድድር ለማቅናት ከፊቷ የሚጠብቋትን የማጣሪያ ጨዋታዎች በድል መወጣት ግድ ይላታል፡፡ ከሩዋንዳ አቻው ጋር በቀጣዩ መስከረም ወር አጋማሽ የደርሶ መልስ መርሀግብር የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤል እና በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ፀጋዘአብ አስገዶም እየተመራ በቢሾፍቱ ከተማ ዝግጅቱን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ የዋና አሰልጣኙ ረዳት በማድረግ አሰልጣኝ ብዙዓየው ጀምበሩን ምርጫው አድርጓል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና ያለፉትን ሦስት አመታት ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ የሆነችው ብዙዓየሁ ብሔራዊ ቡድኑን በመቀላቀል ወደ ሥራ ገብታለች፡፡