ንግድ ባንክ በፍፃሜው ጨዋታ በቪሂጋ ኩዊንስ ተሸንፏል

በሴካፋ ዞን የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ የፍፃሜ ጨዋታ የውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር ክለብ ቪሂጋ ኩዊንስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-1 አሸንፎ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በግማሽ ፍፃሜው የዩጋንዳውን ሌዲ ዶቭስን ካሸነፈበት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ታሪኳ ዴቢሶ እና ትዕግስት ያደታ አርፈው ዓለምነሽ ገረመው እና ሕይወት ደንጊሶ ወደ አሰላለፍ መጥተዋል።

ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከጅማሮ ጎል ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበር። በተለይ ቪሂጋ ኩዊንሶች በትሬዛ ኢንጊሻ አማካኝነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥቃቶችን በመፈፀም መሪ ለመሆን ጥረዋል። በቅድሚያም በአምስተኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርራ በመምታት የግብ ዘቧ ታሪኳ በርገናን የፈተነች ሲሆን ወደ ውጪ የወጣውንም ኳስ ከመዓዘን ሲሻማ በድጋሜ አግኝታ መረብ ላይ ለማሳረፍ ሞክራ ነበር። ከሁለቱ ሙከራዎች በተጨማሪም ቁመታሟ አጥቂ በ7ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተነሳን ኳስ በመጠቀም ሌላ ሙከራ አድርጋ መክኖባታል።

የቪሂጋን ጫና ተቋቁመው ቀስ በቀስ ኳሱን መቆጣጠር የጀመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው እስከ 26ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። እርግጥ ቡድኑ በሎዛ እና መዲና አማካኝነት ለማጣቃት ቢሞክርም እስከ ተጠቀሰው ደቂቃ ድረስ አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ አላደረገም ነበር። በዚህ ደቂቃ ግን አረጋሽ ካልሳ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሯ ለማስቆጠር ጥራ ዒላማውን ስቶ ወጥቶባታል።

ጨዋታው 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ቪሂጋ ኩዊንሶች ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም በፈጣን ሽግግር ወደ ባንክ በማምራት ከቀኝ መስመር የተነሳን ኳስ ጄንትሪክስ ቺካንጋዋ ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ ስትተፋው እንደምንም ታግላ መረብ ላይ አሳርፋዋለች። በበርካታ መስፈርቶች የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት መሪዎቹ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት አሁንም መታተር ይዘዋል። በተለይ ደግሞ ከቀኝ መስመር የሚነሱ ኳሶችን በማዘውተር ባንክ ላይ ጫና አሳድረው ነበር። ነገርግን ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ ከወደ ቀኝ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት ባንኮች ደግሞ አቻ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል ለማምራት የመጨረሻ ዕድል ቢያገኙም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹን ያገባደዱት ባንኮች የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በስምንተኛው ደቂቃ አቻ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ የቅጣት ምት ያገኘው ቡድኑ ዓለምነሽ ገረመው ስታሻማው ቪቪያን ማኮካ በራሷ መረብ ላይ ኳሱን በግንባሯ አሳርፋዋለች። በራሳቸው ጥፋት ግብ ያስተናገዱት ቪሂጋ ኩዊንሶች በ60ኛው ደቂቃ ቫዮሌት ዋንዮንይ ከመስመር ለማሻማት በሚመስል ሁኔታ ወደ ሳጥን በጣለችው ነገርግን የግቡን አግዳሚ ነክቶ በወጣው ኳስ ዳግም መሪ ሊሆኑ ነበር። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ጄንትሪክስ ቺካንጋዋ ሌላ ኳስ ወደ ግብ ልካ የግቡ አግዳሚ በድጋሜ መልሶታል።

ለባንክ ተከላካዮች ፈተና የሆነችው የ20 ዓመቷ ጄንትሪክስ ቺካንጋዋ በ66ኛው ደቂቃም ሌላ ያለቀለት ሙከራ ወደግብ መትታ የነበረ ሲሆን ታሪኳ ግን በጥሩ ቅልጥፍና አምክናዋለች። ይህቺው አጥቂ በ70ኛው ደቂቃም እጅግ ለግብ የቀረበ ኳስ መትታ ለጥቂት ወጥቶባታል። አሁንም ጫናዎች የበዛባቸው የአሠልጣኝ ብርሃኑ ተጫዋቾች በ75ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የግብ የቀረበ ሙከራ በራሳቸው በኩል አድርገዋል። በዚህም ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገን ኳስ ህይወት ደንጊሶ በግንባሯ የሞከረችው ቢሆንም ግብ ጠባቂው ሊሊያን አድናዋለች።


እጅግ ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ቪሂጋዎች በ84 እና 86ኛው ደቂቃም ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። ነገር ግን በጨዋታው ቡድኗን ይዛ ለመውጣት ስትጥር በነበረችው ታሪኳ ኳሶቹ መክነዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ የተጨመሩት አራት ደቂቃዎች ማብቂያ ላይ የመጨረሻ ሙከራቸውን ለማድረግ ወደ ባንክ የፍፁም ቅጣት ምር ያመሩት ቪሂጋዎች በአጨቃጫቂ ሁኔታ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዚህም ታሪኳ ደቢሶ ጥፋት ሰርታ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጄንትሪክስ ቺካንጋዋ ወደ ግብነት ቀይራዋለች። ጨዋታውም በቪሂጋ ኩዊንሶች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ የዋንጫው ባለቤት በመሆን በዋናው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ መሳተፉን አረጋግጧል። በውድድሩ ሁለተኛ የወጣው የኢትዮጵያው ተወካይ ክለብም የፍፃሜ ተፋላሚ በመሆኑ 20 ሺ ዶላር እና ብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።