አዳማ ከተማ ተስፋኛውን አጥቂ ወደ ዋናው ቡድን አሳደገ

ከ17 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ ጎልቶ መታየት የቻለው ተስፋኛው አጥቂ ወደ አዳማ ከተማ ዋናው ቡድን አድጓል።

በመቂ ከተማ የተወለደው እና በ2013 የውድድር ዘመን ለአዳማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ሲጫወት የቆየው ዮሴፍ ታረቀኝ ለአራት ዓመታት የሚያቆየውን ስምምነት ባሳለፍነው ሐሙስ ፌዴሬሽን በመገኘት መፈፀሙን አረጋግጠናል።

በ2013 በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ 28 ጎሎችን በማስቆጠር አቅሙን ያሳየው ዮሴፍ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል መሸለሙ ሲታወስ በቅርቡ በባቱ ከተማ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ባሳየው አቋም የውድድሩ ምርጥ አጥቂ በመባል ተሸልሞ ነበር።

ዮሴፍ ወደፊት ለአዳማ ከተማ በትልቅ ደረጃ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በሊጉ በሚኖራቸው ጨዋታዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠበቃል።