በግዙፉ የባህርዳር ስታድየም ቲፒ ማዜምቤን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ በጨዋታው ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ ያሰባሰበቻቸውን አስተያየቶች እነሆ ብለናል፡-
በሃይሉ አሰፋ
‹‹ ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የምንፈልገውን ውጤት ማግኘት አልቻልንም፡፡ ማሸነፍ የነበረብን ቢሆንም እግርኳስ በምታስበው መንገድ አይሄድም፡፡
‹‹ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ የመልሱን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለብን፡ እንደዛሬው ተጋግዘን የምንጫወት ከሆነ ደግሞ ምንም የሚከብድ ነገር የለውም፡፡ ዋናው እዚህ ራሳችንን በስነልቡናው እንዳዘጋጀነው ለመልሱ ጨዋታም መዘጋጀት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለውም፡፡ እግርኳስ በ90 ደቂቃ የሚወሰን ስፖርት ነው፡፡ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ አለማለፋችንን ለማወቅ ሌላ 90 ደቂቃ ይቀረናል፡፡ ቲፒ ማዜምቤዎች እዚህ ሁለት ጎል እንዳስቆጠሩት እኛም ከሜዳችን ውጪ ተመሳሳዩን የማንፈፅምበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ››
ዘሪሁን ሸንገታ
‹‹ በጨዋታው ማሸነፍ የሚያስችሉ እድሎችን ፈጥረን አሸንፈን መውጣት እንችል ነበር፡፡ ያ ባይሳካልንም በተጫዋቾቻችን የማሸነፍ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ተደስተናል፡፡ በሰራናቸው ስህተቶች ጎሎች ተቆጥረውብን አቻ ብንወጣም በውጤቱ ቅር አልተሰኘንም፡፡ በጨዋታው የቲፒ ማዜምቤ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምን እንደሆነ አይተናል፡፡ እኛም የራሳችንን ድክመት በማሻሻል በመልሱ ጨዋታ አሸንፈን ለማለፍ አንታገላለን፡፡ ››
ሁበርት ቬሉድ – የቲፒ ማዜምቤ አሰልጣኝ
‹‹ጨዋታው እንደጠበቅነው ጠንካራ ፉክክር ታይቶበታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ እኛ ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት እድሎችን ፈጥረናል፡፡ ትንሽ ቅር ያሰኙን በጨዋታው ያስተናገድናቸው ግቦች ብቻ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ቡድን መሆኑን አይተናል፡፡ እንቅስቃሴያቸው ክብር እድንሰጣቸው አድርጎናል፡፡ በቀጣዩ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ቢጠብቀንም አሸንፈን ለማለፍ እጫወታለን፡፡››
የደጋፊዎች አስተያየት
ሶከር ኢትዮጵያ ከጨዋታው በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በጨዋታው ዙርያ ያላቸውን አስተያየት በሰበሰበችው መሰረት አመዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች በቡድናቸው ብቃት መደሰታቸውንና በውጤቱ እንዳልተከፉ ተግረዋል፡፡ የሃገራችን የስፖርት ጋዜጠኞች ለቲፒ ማዜምቤ የተጋነነ ምስል መፍጠራቸው እንዳስከፋቸውም ተናግረዋል፡፡