መከላከያ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ከግብፁ ምስር ኤል ማቅሳ ጋር ባደረገው ጨዋታ ምክንያት ወደ ዛሬ ተላልፎ የነበረው የ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መከላከያን በአዲስ አበባ ስታዲየም አገናኝቶ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ቢኒያም አሰፋ በ30ኛው ደቂቃ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት አጋጣሚ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲሁም ሙሉአለም ጥላሁን ላይ ጥፋት ተሰርቶ ሳሙኤል ሳሊሶ የመታው የቅጣት ምት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ ፌቮ ኢማኑኤል የመለሰበት በመከላከያ በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው፡፡
በ2ኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው ሁሉ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ደከም ያሉ ቢሆንም መከላከያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሸለው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር መሀመድ ናስርን ቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ በንፅፅር ከሌሎቹ የቡድን ተጨዋቾች በተሻለ የንግድ ባንክን ተከላካዮች ለመረበሽ ሲጥር ተስተውሏል፡፡
ሁለቱም ክለቦች ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ ኳስን ወደ ኃላ እና ወደ ፊት እያንሸራሸሩ አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ላይ በማሳለፋቸው እንደተጠበቀው ጨዋታው ሳቢ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደነበረው አየር ቀዝቀዝ ያለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ተስተናግዶበት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡
ውጤቱ ንግድ ባንክን ባለበት ደረጃ እንዲረጋ ሲያደርገው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው መከላከያ ሁለት ደረጃ አሻሽሏል፡፡