የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ በተከታታይ ከአልጄርያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን ከቅዳሜ ጀምሮ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዛሬ ጀምሮም በቀን ሁለት ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምዱን ያደርጋል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ባለፈው ሳምንት ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከቅዳሜ ጀምሮ ልምምድ ያደረጉ ቢሆነም በጉዳት ፣ በግል ጉዳይ ፣ በክለብ ጨዋታዎች እንዲሁም በውጭ ሃገር የሚገኙት ተጫዋቾች ባለመምጣታቸው ምክንያት እስካሁን በተሟላ ሁኔታ ዝግጅት ማድረግ አልቻለም፡፡
የዛሬው ልምምድ
ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምዱን ያደረገ ሲሆን 3 ግብ ጠባቂዎችን ጨምሮ 15 ተጫዋቾች ልምምድ አድርገዋል፡፡ ግብ ጠባቂዎቹ ጠንከር ያለ ልምምድ ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ሌሎቹ ተጫዋቾች ቀለል ያለ ልምምድ በመስራት እና በግማሽ ሜዳ ለሁለት በመከፈል ጨዋታ አድርገዋል፡፡
ትላንት አመሻሽ በሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ ቡድናቸውን ያገለገሉት ሙሉአለም ጥላሁን እና ቢንያም በላይ ቡድኑን የተቀላቀሉ ሲሆን ቢንያም የዛሬውን ልምምድ ሰርቷል፡፡ ሙሉአለም ግን በቦታው ቢገኝም የቡድኑን ልምምድ ቁጭ ብሎ ተመልክቷል፡፡
በዛሬው ልምምድ ላይ የተገኙት ተጫዋቾች ፡ ታሪክ ጌትነት ፣ ለአለም ብርሃኑ ፣ አቤል ማሞ ፣ አስራት መገርሳ ፣ ሱሌማን መሃመድ ፣ ታደለ መንገሻ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ስዩም ተስፋዬ ፣ ያሬድ ባየህ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ዳዊት ፍቃዱ ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ ቢንያም በላይ ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን እና ተካልኝ ደጀኔ
ታፈሰ ተስፋዬ በጉዳት ከቡድኑ ውጭ ሆኗል
የብሄራዊ ቡድን ምርጫ ይፋ በሆነበት እለት አዳማ ከ መከላከያ ጨዋታ ሲያደርጉ በጊዜ ጉዳት አጋጥሞት ተቀይሮ የወጣው ታፈሰ ተስፋዬ ከብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጪ ሆኗል፡፡ በተሟላ ጤንነት የውድድር ዘመኑን መጫወት ያልቻለው ታፈሰ በቻን ዝግጅት ወቅትም ጉዳት አጋጥሞት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት አልተቻለም
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከአልጄርያው ጨዋታ በፊት ከሌሎች የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ጋር የዝግጅት ጨዋታ የማድረግ ፍላጎት ቢኖራቸውም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አሰልጣኙ ያለፉትን ሁለት ወራት ከሞሮኮ ፣ ግብጽ ወይም ቱኒዚያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ቡድናቸውን ለአልጄርያው ጨዋታ ለማዘጋጀት ጥያቄ ቢያቀርቡም አልተሳካም ተብሏል፡፡
ቀሪዎቹ ተጫዋቾች
የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አሉላ ግርማ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ በሃይሉ አሰፋ እና ሳላዲን ሰኢድ ከቻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ መልስ ወደ ቡድኑ የሚቀላቀሉ ሲሆን ሽመልስ በቀለ እና ጌታነህ ከበደ ከግብጽ እና ደቡብ አፍሪካ መጥተው በጥቂት ቀናት ውስጥ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ታውቋል፡፡