ፕሪሚየር ሊግ ፡ ደደቢት ወደ ላይ መውጣቱን ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረገ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢት መከላከያን 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 4ኛነት አሻሽሏል፡፡

ደደቢት አሸናፊ የሆነበትን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ናይጄርያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ሲሆን የመጨረሻዎቹን 15 ደቂቃዎች የታሪክ ጌትነትን በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበት ተከትሎ ግብ ጠባቂ በመሆን ከተመልካቹ አድናቆት ያተረፈበትን አቋም አበርክቷል፡፡

ደደቢት ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ በ31 ነጥቦት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በ9ኛ ቦታው ላይ ረግቷል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የደደቢቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሁለተኛው አጋማሽ የወሰኗቸው ታክቲካዊ ውሳኔዎች ለድል እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ በመጀመርያው 45 በነበረው የቡድኔ የጨዋታ እንቅስቃሴ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የቀየርኳቸው ተጫዋቾች ጨዋታውን ለውጠውት ለድል በቅተናል፡፡ ሳሙኤል ሳኑሚ በልምምድ ሜዳ ላይ ግብ ጠባቂ ሆኖ የሚጫወትባቸው አጋጣሚዎች በመኖራቸው የታሪክን በቀይ መውጣት ተከትሎ የግብ ጠባቂነቱን ቦታ ሸፍኗል፡፡ ሳኑሚ አንድ ተጫዋች ትክክለኛ አትሌት የሚያሰኘውን ብቃት የያዘ ተጫዋች ነው፡፡ ››

በእለቱ የመነጋገርያ ርእስ ሆኖ ያመሸው ሳሚ ሳኑሚ በበኩሉ በልምምድ ሜዳ ያለው የግብ ጠባቂነት ልምድ ኃላፊነት እንዲወስድ እንደገፋፋው ተናግሯል፡፡

‹‹ አሰልጣኛን የመጨረሻ ጨዋታቸው በመሆኑ ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ታግለናል፡፡ በልምምድ ሜዳም ግብ ጠባቂ ሆኜ የምጫወትባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ በመሆኑ ይህንን ኃላፊነት ወስጃለው፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ክብር በማሸነፍም አንድ ታሪክ መፃፍ እፈልጋለሁ፡፡

የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በጨዋታው ዙርያ ለጋዜጠኞች አስተያየት ሳይሰጡ ስታድየሙን ለቀው ወጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *