ዛሬ በ10፡30 በኢትዮጵያ ሆቴል የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እሁድ እለት የሚያደርገውን አመታዊ ሩጫ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና አመታዊ ሩጫ የካምፕ ግንባታ የገቢ ማሰባሰብያ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ወርቅሸት በቀለ ፤ የክለቡ ስራ አመራር አባል አቶ ዳንኤል ዘርአያቆብ ፤ አቶ ፍቅሩ ከበደ የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ፤ አቶ የሱፍ ሞሀመድ የካምፕ ግንባታ ገቢ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ በካምፑ ግንባታ ፣ በሩጫው ዝግጅት እና ተያያዝ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹የካምፕ ስራው ከተጠናቀቀ በኃላ የስታድየም ስራው ይከተላል›› አቶ ወርቅሸት
‹‹ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም በተጀመረው የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ከኮንሰርት 800 ሺህ ብር ፣ በኔክሰስ ነሃሴ 24 ቀን 2006 በኔክሰስ ሆቴል ባዘጋጀነው የእራት ምሽት ላይ 2 ሚልዮን ብር ገቢ አስገብተናል፡፡ በመጪው እሁድ የሚካሄደው አመታዊ የቡና እና የስፖርት ቤተሰቦች የሩጫ ፕሮግራም 3ኛው አብይ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራማችን ነው፡፡ እስካሁን በተጨባጭ 8ሺህ ቲሸርቶች የተሸጡ ሲሆን ከቲሸርቱ 1.2 ሚልዮን ብር ገቢ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን፡፡
የካምፕ ግንባታው ሂደት በአጥጋቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የስትራክቸር ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን የፊኒሺንግ ስራ በቅርቡ እንጀምራለን፡፡ እስካሁን በሂደቱ ውስጥ ድጋፍ ላደረጉልን በሙሉ ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ አላማችን ጉቅ እንደመሆኑ ይህ ስራ ከተጠናቀቀ በኃላ ደግሞ የስታድየም ስራው ይከተላል፡፡››
‹‹ ለቡ አካባቢ ወደፊት የቡና ስፖርት ክለብ ማእከል ይሆናል ›› አቶ ገዛኸኝ
ከጋዜጠኞች የቀረቡትን በርካታ ጥያቄዎች ደግሞ አቶ ገዛኸኝ እና አቶ የሱፍ መሃመድ አብራርተዋል፡፡
‹‹ ወጪውን በተመለከተ የቲሸርት ወጪው 320ሺህ ብር ይጠጋል፡፡ የሜዳልያ ወጪው ደግሞ 280 ሺህ ብር ነው፡፡ በአጠቃላይ 600 ሺህ ብር ወጪ አድርገናል፡፡ ይህ ወጪ ጥቃቅን ወጪዎችን አይጨምርም፡፡ አጠቃለይ ገቢ እና ወጪውን ከፕሮግራሙ መጠናቀቅ በኃላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
ከስፖንሰር ገቢዎች በአጠቃላይ 725 ሺኅ ብር የተገኘ ሲሆን ከንደኛ ደረጃ ስፖንሰሩ ሐበሻ ቢራ 500 ሺህ ብር (በአይነት) ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ስፖንሰሩ ወርቤክ 150 ሺህ ብር ፣ የ3ኛ ደረጃ ስፖንሰሮቹ ብርሃን ባንክ እና ኢንሹራንስ ፣ ጀስቲስ ኮንስራክሽን እና ራስ ሂል ባር እና ሬስቶራንት ደግሞ እያንዳንዳቸው 75 ሺህ ብር ስፖንሰር አድርገዋል፡፡
በመጀመርያ ያሰብነው የመሮጫ ቦታ አመቺ ባለመሆኑ አሁን ከለቡ – ጀሞ አደባባይ – ሚካኤል አደባባይ – ጀርመን አደባባይ አድርጎ ለቡ የሚጠናቀቅ እንዲሆን አደርገናል፡፡ ቦታው ከካምፑ በተጨማሪ የስታድየም ግንባታው ወደፊት የሚከናወንበት በመሆኑ የቡና ስፖርት ክለብ ማእከል ይሆናል ብለን ስለምናስብም ጭምር ነው መነሻ እና መድረሻውን ለቡ ለማድረግ የወሰንነው፡፡
ለዚህ ዝግጅት አዲስ እንደመሆኑ ችግሮች ሊገጥሙን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በየአመቱ እየተጠናከረ ከደጋፊዎቻችን ጋር ይበልጥ የምንተሳሰርበት ፕሮግራም ይሆናል ፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀረው የፊኒሺንግ ስራ በመሆኑ ከአመታዊ ሩጫው የምናገኘውን ገቢ ተጠቅመን በዚህ አመት በማጠናቀቅ በ2008 አ.ም አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ነው ያቀድነው፡፡ ››
በአጠቃላይ ከ8ሺህ በላይ ደጋፊዎች እንደሚሮጡበት የሚጠበቀው ሩጫ እሁድ ሚያዝያ 25 ቀን ይካሄዳል፡፡ በአመዛኙ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቡና ካምፕ አጠቃላይ ወጪም 8.4 ሚልዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን በ2008 አ.ም አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡