በ1960ዎቹ መጀመርያ አመታት የወቅቱ የዲናሞ ኬይቭ አሰልጣኝ የነበሩት ቪክቶር ማስሎቭ የ Diamond Midfieldን በ4-4-2 ፎርሜሽን ውስጥ መጠቀም ጀመረ፡፡ በሃገራችን ብዙም የተለመደ ባይሆንም አልፎ አልፎ ክለቦቻችን ሲጠቀሙበት እናስተውላለን፡፡ አተገባበሩና የተጫዋቾቹ የቦታ አያያዝ ስርአት (positioning discipline) ትክክለኛውን የመዋቅር ይዘት ባይዝም በመጠኑ ሲተገበር እናስተውላለን፡፡
በትናንትናው (እሁድ) እለትም በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሃዬ የሚመራው ደደቢት በ4-4-2 ዳይመንድ ፎርሜሽን በወራጅ ቀጠና የሚገኘው የግርማ ኃ/ዮሃንስ ሙገርን ገጥሟል፡፡ በአንፃሩ ሙገር ሲሚንቶ በተለመደው 4-4-2 ፎርሜሽን ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨርሷል፡፡
(ምስል 1)
የመጀመርያዎቹ 30 ደቂቃዎች
4-4-2 ዳይመንድን ማጥቃትን መሰረት ባደረገ የጨዋታ እቅድ ውስጥ ስንጠቀምበት በሜዳው ቁት የሚኖረው ጥበት (narrowness) እንደ መጀመርያ እንከን ይታያል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስልቱን የሚጠቀሙ ቡድኖች በዳይመንድ ሁለቱ የመስመር ጫፎች የሚገኙ የመስመር አማካዮች (Shutlers) ወደ መስመሩ ተጠግተው እንዲሁም ሁለቱ የፊት አጥቂዎች ወደ መስመር እያለፉ ለsystem ተጠቃሚው የስፋት (width) ጥቅምን ያስገኛሉ፡፡ ጥበቱን ለመቀነሰም ይሞክራሉ፡፡
በትናንትናው ጨዋታ ደደቢቶች በቀኝ መስመር ታደለ መንገሻን እንዲሁም አጥቂወቹ ዳዊት እና ሳኑሚን ከላይ በተገለፀው ሚና በማሳተፍ የአጨዋወት ዘይቤውን ህፀፅ በመጠኑ ሊሸፍኑ ችለዋል፡፡ የመስመር ተከላካዮቹ ስዩም እና ተካልኝ ከፊት ለፊታቸው ያሉትን የመስመር አማካዮች (ታደለ እና ብርሃኑ) በፊት ለፊት የማጥቃት እንቅስቃሴ (overlapping movement) እና ወደ መሃል በመግባት (under lapping) ቡድኑ በመስመሩ ተጋጣሚው ሊፈጥርበት የሚችልበትን ችግር ለመከላከልና መስመሩን ጠጣር (solid) ለማድረግ ሞክሯል፡፡
በሙገሮች የቀኝ መስመር ወደኋላ እጅግ አፈግፍጎ ሲጫወት የነበረው ጌድዮን አካክፖ ለብርሃኑ እና ተካልኝ ሰፊ የመጫወቻ ክፍተትን በመተዉ የመጫወቻ ነፃነት እና ቦታን ሲሰጣቸው ታይቷል፡፡ ብርሃኑ ጌድዮንን በሰው በሰው የመከላከል ዘዴ (man-marking) ጫና በመፍጠር (pressing) በግራው መስመር ካለበት ቦታ ብዙም እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ የሙገሮችን የቀኝ መስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ሊገድብ ችሏል፡፡ በዚሁ መስመር በ33ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የመስመር ሽግግር (flank transition) የመጣን ኳስ የተቀበለው ሳሚ ሳኑሚ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ እና የሊጉ 15ኛ ግቡን ከመረብ አሳርፏል፡፡
(ምስል 2)
የሙገር ተጫዋቾች የሚና ለውጥ
በጨዋታው የመጀመርያ 20 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለቱ የሙገር የፊት መስመር ተሰላፊዎች (ኤፍሬም እና በረከት) ተደጋጋሚ የቦታ ቅይይር ያደርጉ ነበር፡፡ የደደቢትን የተከላካይ መስመር የመከላከል ቅርፅ ለማበላሸትና ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች ሰውን በሰው የመያዝ አጨዋወት ለመፈተን በሚመስል መልኩ የተንቀሳቀሱት በረከትና ኤፍሬም ቡድናቸው ላይ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የሚና እና የቦታ ለውጥም አድርገዋል፡፡
በተለይ ኤፍሬም ወደኋላ ተመልሶ የቀኝ መስመር አማካይነትን ሲረከብ ሙገር በዛ መስር የረሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቻለ፡፡ በመጠኑም የደደቢትን የመስመር የበላይነት የሚቀንስ ለውጥ አመጣ፡፡ በአሰልጣኝ ግርማ የተደረገው ለውጥ የነጠላ ተጫዋቾች የሚና ቅይይር ብቻ ሳይሆን የቡድኑን አጠቃለይ ቅርፅ የለወጠ ነበር፡፡ በ10 ቁጥር ሚና የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ሲያሳርፍ የነበረው ደምሰው ቦጋለ የግራውን የመስመር አማካይነት ተረከበ፡፡ ሄኖክ ፍስሃ ደግሞ ወደ ቀኝ መስመር ተሻገረ፡፡ ይህ ሙሉ የመዋቅር ለውጥ የተጋጣሚን የመስመር ጫና መቀነስ ከማስቻሉም በላይ በቀጥተኛ አጨዋወት (direct play) ላይ የተመሰረተውን የሙገር ጨዋታ ይበልጥ አነቃቅቶታል፡፡ የተሳኩ ባይሆኑም በርካታ የግብ ማግባት ሙከራዎች የተከናወኑትም ከዚህ ለውጥ በኋላ ነበር፡፡ በእርግጥ በአጥቂውና በአማካዩ መካከል ያለው መስመር (ክፍተት) ይበልጥ ቢሰፋም ቡድኑ (ሙገር) የተሻለ የተንቀሳቀሰበትን አማራጭ ፈጥሮለታል፡፡
(ምስል 3)
የደደቢት የተደራጀ የተከላካይ መስመር (organized defense)
የዳይመንድ አማካይ ክፍል በሚጠቀመው ቡድን ላየ የሚፈጥረውን የስፋት (width) ችግር ለመቅረፍ ደደቢቶች የተጠቀሙት ስልት ዋጋ ያስገኘላቸው ይመስላል፡፡ ሰውን በሰው በመያዝ አተገባበር እና የሙገሮችን የአግድሞሽ መስመሮች በማራራቅ (በተለይ በአጥቂውና በአማካዩ መካከል ያለውን ክፍተት በመለጠጥ) በተጋጣሚያቸው ሜዳ ገድበው ይዟቸዋል፡፡ ታደለ እና ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ኄኖክ ኢሳይያስ ወደኋላ በማፈግፈግ መስመሮቻቸውን ለመሸፈን ሞክረዋል፡፡
ሳምሶን ጥላሁንም በሜዳው ቁመትና ወርድ እየተንቀሳቀሰ ሰውን ባማከለ እንቅስቃሴ (man-oriented movement) የተጋጣሚውን የማጥቃት አማራጭ ለመገደብ ሞክሯል፡፡ አጥቂዎቹ ዳዊት እና ሳኑሚም ወደ መስመሮች በመጠጋት ፉልባኮቹ ሚፍታ እና ተክለፃዲቅን የፊት ለፊት እንቅስቃሴ ለመግታት ከመቻላቸውም በላይ ለሳምሶን ጥላሁን ሰፊ ቦታን በመስጠት ኋለኛውን የሙገር መስመር መፈተን የሚያስችል አማራጭ ፈጥረዋል፡፡
(ምስል 4)