በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደደቢት አቻ ተለያይቶ የቻምፒዮንነት ተስፋውን ሲያጨልም ሙገር ሲሚንቶ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ላይ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡
አዲስ አበባ ላይ በ9 ሰአት ዳሽን ቢራን ያስተናገደው ደደቢት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ ዳሽን ቢራ የተሸ ግዛው በ9ኛው እና14ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ግቦች 2-0 ቢመራም ሳሙኤል ሳኑሚ በ44ኛው ደቂ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁን በ53ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ባሳረፋት ግብ 2-2 አቻ መሆን ችለዋል፡፡ በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች እና ውጥረት በተሞላበት እንቅስቃሴ በታጀበው ጨዋታ የእለቱ አርቢቴር ለሁለቱም ቡድኖች የፍፁም ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን አስራት መገርሳ ሜዳ ውስጥ ባሳየው ያልተገባ ባህርይ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደውታል፡፡ ደደቢት የአቻ ውጤቱን ተከትሎ የቻምፒዮንነት ተስፋው ጨልሟል፡፡ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭን ካሸነፈም የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱን ያረጋግጣል፡፡
ከጨዋታው በኋላ የደደቢቱ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሃዬ የግብ እድሎችን ወደ ግብነት አለመቀየራቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በጨዋታው መጀመርያ በትኩረት ማጣት ምክንያት ግቦች ተቆጥረውብናል፡፡ በሂደት ወደ ጨዋታው ሪትም በመግባታችን ግቦች አስቆጥረን አቻ ሆነናል፡፡ ከግቦቹ በኋላ ጫና ፈጥረን ብንንቀሳቀስም ለመሳት የሚከብዱ የግብ እድሎችን አምክነናል፡፡ ››
የዳሽኑ አሰልጣኝ ካሊድ መሃመድ በበኩላቸው የዳኛው ውሳኔዎች ውጤት እንዳሳጣቸው ገልፀዋል፡፡ ‹‹ ጨዋታው ውጥረት የበዛበት ቢሆንም ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር፡፡ የቡድን መንፈሳችን ጥሩ ነበር፡፡ የዳኝነት ተፅእኖ ውጤታችንን አስጠብቀን እንዳንወጣ አስተዋፅኦ አድርጎብናል ›› ብለዋል፡፡
ወደ ሃዋሳ ያቀናው ሙገር ሲሚንቶ ባልተጠበቀ የ2-0 ድል ተመልሷል፡፡ ከሳምንት በፊት የመውረዱ ነገር እርግጥ የሚመስል የነበረው ሙገር አሁን ከኤሌክትሪክ በ1 ነጥብ ብቻ አንሶ በኤሌክትሪክ ላይ ጫና ማሳደር ጀምሯል፡፡
ባንክን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 2-0 ተሸንፏል፡፡ ፊሊፕ ዳውዚ እና ሲሳይ ቶሊ የባንክን የድል ግቦች ያስቆጠሩ ሲሆን ናይጄርያዊው አጥቂ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች መጠን ወደ 16 አሳድጓል፡፡
አዳማ ላይ ኤሌክትሪክ በአዳማ 1-0 ተሸንፎ የመውረድ ጫና ውስጥ ገብቷል፡፡ የ2 ጊዜ የሊጉ ቻምፒዮኑ ኤሌክትሪክ ከሙገር ያለው የነጥብ ልዩነት 1 ብቻ ሆኗል፡፡
በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን 1-0 አሸንፎ ከ7 ጨዋዎች በኋላ የመጀመርያ ድል እና ግብ አስመዝግበዋል፡፡ ከግብ መንገዱ ርቆ የሰነበተው ቢንያም አሰፋ በ69ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅታት ምት የቡናን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ሊጉ ነገ ሲቀጥል ቅዱ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ11፡00 ሲፋለሙ መውረዱን ያረጋገጠው ወልድያ መልካ ቆሌ ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ ፈረሰኞቹ ይህን ጨዋታ ካሸነፉ ለ27ኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡