በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት አስቀድሞ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ወልድያ መልካ ቆሌ ላይ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 3-2 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ወደ ሜዳ የገቡት ወልድያዎች ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው 1 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ቡድኑን የተቀላቀለው ፍፁም ደስይበለው ወልድን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
የመጀመርያው አጋማሽ የግብ ሙከራዎች እምብዛም ባልታየበት ሲሆን በ33ኛው ደቂቃ በጨዋው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እንዳለ ከበደ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ ባስቆጠራት ግሩም ግብ ሲዳማ ቡናን አቻ አድርጓል፡፡
በ35ኛው ደቂቃ ወልድያዎች በድጋሚ መሪ የሚያደርጋቸውን ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ግቧ ሳትፀድቅ ቀርታለች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያዎች የተጫዋች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ታደለ ባይሳን በሳሙኤል ደግፌ ቀይረዋል፡፡ በ52ኛው ደቂቃ ወልድያዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ሲዳማዎች በአግባቡ ከግብ ክልል ባለማራቃቸው አምበሉ ፍሬው ብርሃን አግኝቶ ወልድያን በድጋሚ መሪ የምታደርገውን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ይህች ግብ ለተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ፍሬው በውድድር ዘመኑ 5ኛ ግብ ነች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወልድያ ቋሚ አሳላለፍ ውስጥ ሰብሮ መግባት የቻለው ግብ ጠባቂው ቢንያም በጨዋታው 55 እና 60ኛ ደቂቃዎች ላይ ያለቀላቸው የግብ እድሎችን በግሩም ሁኔታ በማክሸፍ ወልድያ ተጨማሪ ግ እንዳይቆጠርብት ሲጥር ታይቷል፡፡
በ79ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አብይ በየነ ከግራ መስመር ከወሰኑ ማዜ የተገኘችውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ወልድያን 3-1 እንዲመራ አስችሏል፡፡ ወልድያ በውድድር ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ 3 ግቦችን በተጋጣሚዎቹ ላይ ማሳረፍም ችሏል፡፡
በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ አንጋፋው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ ሲዳማ ቡናን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው በወልድያ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ድሉን ተከትሎ ወልድያ አስቀድሞ መውረዱን ቢያረጋግጥም ነጥቡን ወደ 15 ከፍ አድርጓል፡፡