የአሰልጣኞች አስተያየት | አርባምንጭ ከተማ 2-1 ባህር ዳር ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለማሸነፋቸው

እግዚአብሔር ይመስገን ፤ እግዚአብሔር ረድቶናል። ዛሬ የምፈልገውን ዓይነት ብዙ ነገሮች ስላየሁ መብለጥ በምንፈልገው ልክ በልጠናል ብዬ አስባለሁ። ቡድኑ ወደምንፈልገው ዓይነት ቅርፅ እየመጣ መሆኑ መልካም ነው።

ስለፀጋዬ አበራ ቅያሪ

በተወሰነ መልኩ ያየኋቸው ችግሮች ነበሩ። የእኛ ቡድን የተመጣጠነ በድን ነው። በመሆኑም ክፍተቶቹን የማረሙ ሥራ የተሳካ ነበር።

ውጤቱ ቡድኑ ላይ ስለሚፈጥረው መነሳሳት

ለአሸናፊነት አንገመትም ፤ ሁለተኛ ደረጃን ይዘን ነው የምንገባው። ካደረግናቸው አራት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፈን አንዱን ነጥብ ተጋርተናል። ይሄ በደንብ ያነሳሳል። እያንዳንዱን ጨዋታ ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንጫወታለን። ማንኛውም ቡድን ይሁን ሙሉ ነጥብ ይዘን ለመውጣት እንገባለን።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለቡድናቸው እንቅስቃሴ

ዛሬ ቡድኔ ጥሩ ነበር ማለት አልችልም። የተወሰኑ ጉድለቶች ነበሩ። ምንም እንኳን የተቆጠሩብን ግቦች ከቆሙ ኳሶች ቢሆንም እነዛ ላይ በጣም ጥንቃቄ ማደረግ እንዳለብን ያሳየን ጨዋታ ነው። በቀላሉ የምንሰራቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል። እነዚህን ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን።

ሊጉን የመምራት ዕድል ስለማምከናቸው

ሁሉም ፍላጎቱ የላይኛውን ደረጃ ለመያዝ ነው። እኛም ከጨዋታ በፊት ያንን ደረጃ አስጠብቆ ለመውጣት ተነጋግረን ነው የገባነው። ከዛም ጉጉት የተነሳ አንዳንዴ ጨዋታ እንደታሰበው አይሆንም። ዞሮ ዞሮ እንደዚህ ጥሩ ሳትሆን የምትውልበት ጊዜ ይኖራል። እንደትምህርት ወስደነው በሚቀጥለው አስተካከልን ለመምጣት እንሞክራለን።

ስለስህተቶች

ጥቃቅን የተጫዋቾች የተናጠል ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል እንጂ እንደቡድን አርባምንጭ ተጫውቶ በልጦ ያገባብን ጎል የለም። እነዛን ስህተቶች የግድ ማረም ያስፈልጋል።

የሚፈልጉትን የመጫወቻ ክፍተት ስለማግኘታቸው

በመጀመሪያው አጋማሽ አግኝተናል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን እነዛን ክፍተቶች በሚገባ መጠቀም አልቻልንም። ለዚህም ነው ሁለቱን የክንፍ አጥቂዎች ቀይረን በሌሎች ተጫዋቾች ተክተን በመጠኑም ቢሆን ጫና ለመፍጠር የሞከርነው እንጂ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ተጠቅመናል ብዬ አላስብም።