ሪፖርት | በመጀመሪያው አጋማሽ ልዩ የነበረው አዲስ አበባ ከተማ የሊጉን መሪ ፋሲል አሸንፏል

ሳቢ እንቅስቃሴ የታየበት የአዲስ አበባ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ሦስት ግቦች ተስተናግደውበት አዲስ አበባ ከተማን ባለ ድል አድርጓል።

በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከመከላከያ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል የሸመቱት አዲስ አበባ ከተማዎች ከድል ጋር ከታረቁበት ጨዋታ ኢያሱ ለገሠን በሳሙኤል አስፈሪ፣ ሳዲቅ ተማምኝ በኤሊያስ አህመድ እንዲሁም ብዙአየሁ ሰይፉን በእንዳለ ከበደ ለውጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ተጋጣሚያቸው የነበረውን ጅማን አራት ለምንም አሸንፈው የመጡት ፋሲል ከነማዎችም አብዱልከሪም መሐመድ፣ አስቻለው ታመነ እና ሽመክት ጉግሳን በሰዒድ ሀሰን፣ ይሁን እንዳሻው እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

አስገራሚ እንቅስቃሴ ማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሪያ ሙከራ ተደርጎበታል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሪችሞንድ አዶንጎ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ መትቶት ወደ ላይ ወጣበት እንጂ አዲስ አበባ ከተማ በጊዜ ቀዳሚ ሊሆን ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ አዲስ አበባዎች በሙሉቀን አዲሱ አማካኝነት በተመታ የርቀት ኳስ ሌላ ሙከራ አድርገው ተመልሰዋል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ በአንፃሩ የተሻሉ የሚመስሉት ፋሲሎች እስከ 44ኛው ደቂቃ ድረስ የአዲስ አበባን ግብ ጠባቂ ሳይፈትኑ ጨዋታው ቀጥሏል።

ጨዋታው ሩብ ሰዓት ሲሞላው ደግሞ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎች በማድረግ አጀማመራቸውን ያሳመሩት አዲስ አበባዎች ሌላ ያለቀለት አጋጣሚ ፈጥረዋል። በዚህም እንዳለ ከበደ የፋሲሉ የመሐል ተከላካይ ያሬድ ባየህ የተሳሳተውን ኳስ ለሪችሞንድ ሰጥቶት ወደ ግብ ቢሞከርም ሜኬል ሳማኪ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። ጨዋታው 21ኛው ደቂቃ ላይ ግን አዲስ አበባዎች የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። በዚህም ፍፁም ጥላሁን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከደቂቃዎች በፊት ጥሩ ኳስ ያመከነው ሳማኪ በወረደ ውሳኔ ኳሱን በእግሬ አወጣለሁ ሲል ተጨርፎ አቅጣጫ ሲቀይር ሪችሞንድ አዶንጎ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ አግኝቶት ግብ አድርጎታል። ግቡ ከተቆጠረ በደቂቃ ልዩነት ደግሞ በድጋሜ ኤሊያስ አህመድ ፍጥነት እና የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን እየገፋ ይዞት የገባውን ኳስ ለፍፁም አቀብሎት የነበረ ሲሆን ፍፁም ወደ ጎል የመታውን ኳስ ግን ስራዎች የበዙበት ሳማኪ ሁለተኛ ግብ ከመሆን አድኖታል።

ተረጋግተው መጫወት የተሳናቸው የሚመስሉት ፋሲል ከነማዎች ቀስ እያሉ ወደ ጨዋታው በመግባት ለመጫወት እና ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት ቢጥሩም እጅግ በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲጫወቱ የነበሩትን አዲስ አበባዎች ማስከፈት ሳይችሉ ቀርተዋል። ይባሱኑ በ39ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸው ፈተናቸው ብሷል። በዚህ ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኤሊያስ አህመድ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከመሐል ሜዳ እየገፋ የሄደውን ኳስ ለሪችሞንድ አቀብሎ በድጋሜ ቦታ ከያዘ በኋላ ተቀብሎ ተከላካዩ ከድር ኩሊባሊን በማለፍ የቡድኑን መሪነት ከፍ አድርጓል።

ያልጠበቁት ፈተና ሜዳ ላይ የገጠማቸው ፋሲል ከነማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ለመጀመሪያ ጊዜ ለግብ የቀረቡበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል። በዚህም ቡድኑ ያገኘውን የመዓዘን ምት ፍቃዱ ዓለሙ ለመጠቀም ጥሮ ወጥቶበታል። በአጋማሹም ፋሲል ከነማ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ ወጥቷል።

ከሁለተኛውን አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ ተግተው መጫወት የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች በ49ኛው ደቂቃ በበረከት ደስታ አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ሰንዝረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር ይዘዋል። አሠልጣኝ ሥዩም ከበደም የተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ የማጥቃት ሀይላቸውን ለማሻሻል ጥረዋል። በተለይ ደግሞ በ56ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ላይ የተሰለፈው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ሳጥን ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ተቀይቶ ወደ ሜዳ የገባው ሳሙኤል ዮሐንስ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የግብ ዘቡ ዳንኤል ተሾመ ሲተፋው በረከት አግኝቶት መረብ ላይ ሊያሳርፈው ነበር።

በዚህኛው አጋማሽ በደንብ ተሻሽለው የቀረቡት ፋሲሎች ከደቂቃ ደቂቃ እድገት እያሳዩ በመምጣት በ62ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ሳሙኤል ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ በግንባሩ ግብ አድርጎታል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ መጫወት ያልቀጠሉት መሪዎቹ አዲስ አበባዎች ፍላጎታቸው ትንሽ ወረድ ብሎ በመገኘቱ ጫናዎች በርትቶባቸዋል። በ78ኛው ደቂቃም ፍቃዱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ አምሳሉ ጥላሁን በሞከረው የቅጣት ምት ሁለተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በቀሪ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ፋሲሎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው የሚወጡበትን ሁነት ለመፍጠር ቢንቀሳቀሱም ሳይሳካላቸው ሦስት ነጥብ አስረክበው ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን ስድስት በማድረስ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ በጊዜያዊነት ወደ አምስተኛ ደረጃ ሲሸጋገር የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ደግሞ ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሰበሰበው ዘጠኝ ነጥብ ባለበት አንደኛ ደረጃ ቀጥሏል።