ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ነገ 12 ሰዓት ላይ የሚደረገውን ተጠባቂ ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።

ያለፉት አራት የጨዋታ ሳምንታት አዎንታዊ ውጤት ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ቡና ያሸነፋቸውን የጨዋታ ቁጥሮች ወደ አምስት ለማሳደግ ከሌላኛው ሁለት ተከታታይ የድል ውጤቶች በኋላ ከሚመጣው ሀዲያ ሆሳዕና ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀው እሙን ነው።

ወልቂጤን አንድ ለምንም ባሸነፉበት ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር እንዲሁም ዒላማውን በጠበቀም ሆነ ባልጠበቀ የግብ ሙከራ ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ የታዩት ኢትዮጵያ ቡናዎቸዎች እንደተለመደው ኳስ መስርቶ ለመውጣት ግን ሲፈተኑ ነበር። በለተይ ወልቂጤዎች እንደ ቅፅል ስማቸው ታታሪ ሰራተኛ በመሆን የኳስ ቅብብሎቻቸውን ገና ከግብ ክልላቸው ሳይርቁ ለማክሸፍ ሲጥሩ ታይቷል። ምንም እንኳን ቡድኑ በዚህ ረገድ ለበርካታ ጊዜያት ሲቸገር ብናይም በጨዋታው ዋጋ አለመክፈሉ ጥሩ ነው። ይህ በጨዋታው የታየውን የቡድኑን የአደባባይ ሚስጥር የሆነው ክፍተትም ሀዲያዎች ለመጠቀም እንደሚፍጨረጨሩ ይገመታል። በተለይ ከወገብ በላይ የሚገኙት ፈጣን አጥቂዎች በሰው በሰው አልያም በቦታ ማርክ እያደረጉ የቡድኑን የሀሳብ መነሻ (ኳስ ቁጥጥር) ገና ከጅምሩ ለማበላሸት እና አደጋ እምብዛም ከግቡ ሳይርቁ ለመፍጠር ሊያስቡ ይችላሉ። ይህንን ተከትሎ አሠልጣኝ ካሣዬ ለዚህ ክፍተት ተገቢ መፍትሄ ይዞ መቅረብ ይጠበቅበታል።

ቡና አንዳንድ እየተቸገረባቸው በነበራቸው ጨዋታዎች ላይ ከዋነኛ የአሠልጣኙ ሀሳብ እያፈነገጠ ሲንቀሳቀስ ይታያል። ባለፈውም ወልቂጤን ሲያሸንፉ በመልሶ ማጥቃት ግብ አስቆጥረዋል። ይህ ደግሞ ነገም መሰል ቅፅበቶችን ለማግኘት ፍላጎት እንዲያድርበት ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ ውጪ ያለፉትን ጨዋታዎች የዊሊያም ወደ አጥቂው መስመር ተለጥፎ መጫወት ሰብሮ ለመግባት እና ሌላ የጎል ምንጭ ለማግኘት እያስቻለው ነው። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ ታታሪነት ያላቸውን የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ፈጣን አጨዋወት ማምከኛ አማራጭ እንደሚሻ መናገር ይቻላል።

እንደ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና አራት ባይሆንም ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነገ የሚጫወቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ከረጅም ጊዜያት በኋላ ያገኙትን የአሸናፊነት መንገድ ላለማጣት እና አሁንም በሰንጠረዡ ሽቅብ ለመጓዝ በሚያደርጉት ሂደት በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ከሚገኘው ቡና ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃቸው ይታመናል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ከቀደሙት ስድስት ጨዋታዎች ካስቆጠሩት ግብ ከእጥፍ በላይ (5) ያገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወሳኝ ግብ አግቢ ያገኙ ይመስላል። ሀብታሙ ታደሰ! የተጫዋቹ ብቃት የቡድኑን ግብ የማግባት ችግሩን የተቀረፈ ቢያስመስለውም ግን አሁንም ተጨማሪ ግብ አግቢዎች ሀዲያ ያስፈልጉታል። ተጫዋቹ ግን በነፃነት ሳጥን ውስጥ እንዲያሳልፍ መደረጉ እና ከተከላካዮች እያፈተለከ የሚወጣበት ፍጥነቱ እንዲሁም ቦታ አያያዙ ለተከላካዮች አደጋ ነው። ሀዲያዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ያደረጉት የድሬዳዋ ጨዋታ ድል ደግሞ ከመመራት ተነስቶ መሆኑ ወደሚፈልጉት የማሸነፍ ስነልቦና እየመጡ መሆኑን ያሳያል። ይህ ቢሆንም ግን አሁንም ሌላ ከበድ ያለፈተና ነገ ይገጥማቸዋል።

በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ሀዲያ ከኋላ ሲከላከል አምስት መሆኑ ቡናን ለመከላከል በቁጥር ደረጃ ጥሩ ነው። ግን ድሬዎች በመስመር ሰብረው የገቡባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች ለነገው ጨዋታ ማስጠንቀቂያ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህ ውጪ ኳስ መያዝ ቢፈልጉም ከቡና ይልቅ በቶሎ ሳጥን ውስጥ የመድረስ ፍላጎት ይታይባቸዋል። ለዚህም ሀይላይን (ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ የሚከላከል) ከሚሰራ ቡድን ጋር ከጀርባ ኳስ የመጣል እና የግብ ዕድል የመፍጠር ስኬት ምልክት አሳይቷል። በተለይ ደግሞ ከሳምሶን ጥላሁን። ስለዚህም ነገ እንደ ቡና የኳስ ቁጥጥር ፍላጎት እንደሚኖራቸው ባይታሰብም ከተከላካይ ጀርባ እና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የሚገኙ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም እንደሚጥሩ ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ከላይ እንደጠቀስነው የቡናን የኳስ ጅማሮ ሂደትም በተወሰነ ደረጃ በማደናቀፍ የግብ ምንጭነት ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡና የሚኪያስ መኮንን እና ሬድዋን ናስርን ግልጋሎት በነገው ጨዋታም የማያገኝ ሲሆን የግብ ዘቡ በረከት አማረ ግን ከደረሰበት መጠነኛ ጉዳት እንዳገገመ ተነግሮናል። ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ እና ተከላካዩ መላኩ ወልዴን በጉዳት ምክንያት ሲያጣ የመስመር ተጫዋቹ ኢያሱ ታምሩ መግባት ደግሞ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ከዚህ ውጪ ብርሃኑ በቀለም ከጉዳቱ አገግሟል።

12 ሰዓት የሚጀምረውን ፍልሚያ ለሚ ንጉሴ እንደሚመሩት አውቀናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሦስቱን ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 2-1 አሸንፏል። በአንዱ ግንኙነታቸው ደግሞ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ቴዎድሮስ በቀለ – ሥዩም ተስፋዬ

ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን

ያብቃል ፈረጃ – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳ

ቃለዓብ ውብሸት – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ አርፊጮ

ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ኢያሱ ታምሩ

ዑመድ ኡኩሪ – ሀብታሙ ታደሰ