ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከሁለተኛው ሳምንት በኋላ የራቀውን ድል አግኝቷል

በ9ኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየት ሊግ የዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር ወላይታ ድቻን 2-0 አሸንፏል።

ተጋጣሚዎቹ ከመጨረሻ ጨዋታቸው በተመሳሳይ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። ሲዳማ ቡና ከመከላከያው ጨዋታ ምንተስኖት ከበደ እና ብሩክ ሙሉጌታን በሀብታሙ ገዛኸኝ እና ደግፌ ዓለሙን ተክቷል። በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ጉዳት ላይ የነበረው ስንታየሁ መንግሥቱ እና መልካሙ ቦጋለ በምንይሉ ወንድሙ እና አንተነህ ጉግሳ ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ወላይታ ድቻ ኳስ ተቆጣጥሮ በሲዳማ ሳጥን አቅራቢያ ጫና ሲፈጥር ታይቷል። በያሬድ ዳዊት አማካይነት ከሳጥን ውጪ የተደረጉት እና ወደ ላይ የተነሱ ሁለት ሙከራዎችንም አስመልክቶናል። ሆኖም ቀስ በቀስ ሲዳማዎች ወደ ጨዋታው ምት ሲገቡ የወላይቻ ድቻ ጥቃት እየከሰመ መጥቷል። ይልቁኑም ሲዳማዎች ቀሪውን የአጋማሹን ጊዜ ሙሉ ብልጫ ወስደው የጨዋታው ፍሰት ከግብ ክልላቸው ርቆ እንዲከወን አድርገዋል።

ሲዳማዎች የመስመር ተከላካዮቻቸውን በማጥቃት ላይ በማሳተፍ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም በድቻ ላይ ሰፊ ጫና ፈጥረዋል። በተለይም ከቀኝ መስመር በማሻገር ይገዙ ቦጋለን ያማከሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን ያደርሱበት የነበረው መንገድ ለብልጫቸው ማሳያ ነበር። 19ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲደረግ ፍሬው ሰለሞን ከሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ ጋር የተቀባበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሞክሮ ወንድወሰን አሸናፊ አውጥቶበታል። ይህንን ተከትሎ መሀሪ መና ያሻማውን የማዕዘን ምትም ይገዙ በቀጥታ መትቶ በድጋሚ ወንደወሰን ወድኖበታል።

ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ የሲዳማዎች ጥቃት ይበልጥ ተጠናክሮ ሲቀጥል በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት የነበራቸውም ዕቅድ አልሰምር ያላቸው ድቻዎች በራሳቸው ሜዳ ላይ ለመቆየት ተገደዋል። 34ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ከቀኝ ያሻገረውን ኳስ በግራ ሳጥን ውስጥ የተገኘው መስመር ተከላካዩ መሀሪ መና ከጠባብ አንግል ወደ ግብ ሞክሮ ወንድወሰን አድኖበታል። ቀጣዩ የሲዳማዎች ሙከራ ግን በግብ ጠባቂው ሊመለስ አልቻለም። 39ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ሲያርቁ ዳዊት ተፈራ መልሶ ወደ ሳጥን አሻግሮት ጊትጋት ጉት የጨረፈለትን ሀብታሙ ገዛኸኝ ግብ አድርጎታል።

ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተን አጋማሽ ያሬድ ዳዊት ሀብታሙ ገዛኸኝን ከኳስ ውጪ የገፈተረበት ፣ ተክለማሪያም ሻንቆ ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጁ ይዟል በሚል የቅጣት ምት የተሰጠበት እንዲሁም ሲዳማዎች በቁጥር ብልጫ በወላይታ ድቻ ሜዳ ሲገቡ የአርቢትሩ የአጋማሹ መቋጫ ፊሽካ የተሰማበትን የመሰሉ ተጨማሪ ትኩረት ሳቢ ሁነቶችን ያስመለከተን ሆኖ አልፏል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ግብ አግኝቷል። ድቻዎች የሲዳማን ረጅም ኳስ ወደ ግራ ሲያርቁ ኳስ ያገኘው ፍሬው ተከላካዮችን አታሎ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ይገዙ ቦጋለ በቀጥታ መትቶ አስቆጥሯል። ይገዙ 53ኛው ደቂቃ ላይም ከሀብታሙ በደረሰው ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሌላ ግብ ማስቆጠር የሚችልበትን አጋጣሚ አምክኗል።

ከዕረፍት መልስ ምንይሉ ወንድሙን ቀይረው ያስገቡት ወላይታ ድቻዎች በሁለት አጥቂዎች ወደ ፊት የመግፋት ምልክት ቢታይባቸውም የሲዳማዎች የመከላከል ሽግግር በቀላሉ ክፍተት የሚሰጣቸው አልሆነም። ይልቁኑም ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ እንጂ ሲዳማዎች ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን አግኝተው ነበር። 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች በዚህ ረገድ ተሳክቶላቸው ሀብታሙ ገዛኸኝ በመልሶ ማጥቃት ነፃ ዕድል ቢያገኝም ሙከራው በወንድወሰን ድኖበታል።

ቀጣዩ ለጎል የቀረበ ሙከራ 76ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ድቻዎች ከሜዳቸው ለመውጣት የጀመሩትን ኳስ ያቋረጡት ሲዳማዎች ሀብታሙ ከይገዙ ተቀብሎ ባደረገው ሙከራ ለሦስተኛ ግብ ቢቃረቡም የግቡ ቋሚ ከልክሏቸዋል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ጠንቀቅ ብሎ የመልሶ ማጥቃት ባህሪን ሲላበስ ወላይታ ድቻዎች ግብ ለማግኘት ረጅም ኳሶችን ወደ ሲዳማ ሳጥን በማድረስ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረዋል። አሁንም የተሻለው ሙከራ የታየው ግን በሲዳማ በኩል ሲሆን 90ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት በቋሚው ስር ወጥቷል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በሲዳማ 2-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ባስመዘገበው ድል ነጥቡን 11 አድርሶ ከነበረበት 14ኛ ደረጃ ወደ 9ኛነት ከፍ ብሏል።