​የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 2-0 ወላይታ ድቻ

ከዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የተሰጠው የአሰልጣኞች አስተያየት እንዲህ ይነበባል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለቡድኑ የአጨራረስ ብቃት

ካደረግናቸው ሙከራዎች ብዛት አንፃር ጥሩ የሚባል አይደለም። ግን ከነበርንበት ደረጃ አንፃር ፣ ባለፉት ጊዜያቶች ከነበረብን ውጥረት አንፃር ሲገለፅ ዛሬ 2-0 ጥሩ ነው። በተለይ በተለይ አጥቂዎቻችን ጎል ማግባታቸው በራሱ በራስ መተማመን ይፈጥርላቸዋል  ብዬ አስባለሁ።

ስለቡድኑ እንቅስቃሴ 

ዛሬ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። አንደኛ ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ጥሩ ነው። ከዚህ በላይ ወደ ጎል የሄዱበት መንገድ በጣም ጥሩ ነበር። ያው ቁጥሮቹ ይመሰክራሉ ፤ ወደ 18 ጊዜ ሞክረናል። ሁለት ብረት መልሶብናል ያለቁ የሚባሉ ኳሶችም ተስተዋል። ከዚህም በላይ መሆን ይችል ነበር። ዛሬ በአጠቃላይ በእንቅስቃሴው በጣም ደስተኛ ነኝ። ብዙ ነገሮችን መልስ የሰጠ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ያለደጋፊ ስለማሸነፋቸው

በእርግጥ ጫና አለ ፤ ባለፈው ገጬዋለሁ። ልጆቹ አንዳንዴ የሚሳሳቱት ስህተት ጫና ለመቋቋም ባለመቻል ነው። ነገር ግን እኛ ደጋፊ ያስፈልገናል። ደጋፊያችን ከጎናችን ነው ብለን ነው የምናስበው። ምንጊዜም ቢሆን ሲዳማ በጣም ጥሩ ደጋፊ ያለው ስለሆነ ወደፊትም ከደጋፊያችን ጋር ሆነን መጫወትን ነው የምንመርጠው። በተወሰነ መልኩ የሥነልቦና ጫናውን ቀርፈናል ብዬ ነው የማስበው። በቀጣይ ከደጋፊዎቻችን ጋር ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን ብዬ አስባለሁ።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ስለውጤቱ

እንደውጤት ተከታታይ ሦስት ጨዋታ ተሸንፈናል። በዕውቀት ስንገመግመው ደግሞ ምክንያቱ ምንድነው በሚል ነው የምናየው። የእኛ ቡድን ምርጥ 11ጥሩ ነው። ወደ ሙሉ ስብስቡ ጥራት ስንሄድ ግን ወጣት ተጫዋቾች ናቸው ያሉት። በሌላው ቡድን ስናይ ደግሞ ተቀይረው የሚገቡ ተጫዋቾች ውጤት ይቀይራሉ። እኛ እንግዲህ በሦስቱ ጨዋታዎች ጠንካራ ቡድኖች አጋጥመውናል። በዚህ ላይ ከምርጥ 11 ተጫዋቾች በጉዳት ሲወጡብን እየተቸገርን ነው ያለነው። ስብስባችንን መፈተሽ አለብን ብዬ አስባለሁ። ዞሮ ዞሮ ማረም በምንችለው እናርማለን። ማስተካከል ካለብን ደግሞ በጋራ ተወያይተን እናስተካክላለን። ይህን ያህል የወረደ ቡድን አይደለም ያለን። ነገር ግን ሁለተኛው ግብ የገባበት ፍጥነት ሁለተኛው አጋማሽ አስተካክለን ለመምጣት ባሰብነው ልክ አልሄደልንም። ወደ ሪትሙ ሳንገባ ነው የገባብን። ለዛሬ ሽንፈታችን አስተዋፅዖ ነበረው ብዬ እገምታለሁ።

ስለአጥቂዎች ጉዳት 

በቡድናችን ሁለት አጥቂዎች ናቸው ያሉት ፤ ሁለቱም ጉዳተኞች ናቸው። ምንይሉም ከነጉዳቱ ነው ያስገባሁት ፤ እሱም ምርጥ 11 ውስጥ የነበረ ተጫዋች ነው።  ሥንታየሁም በዚህ ሳምንት ልምምድ አላሟላም። ሌላ አማርጭ ስላልነበር ነው እነሱን ይተጠቀምነው። አማካይ ክፍል ላይ ቢሆን ወደ ወጣቶቹ ትሄዳለህ። ከፊት ግን የሰው ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ እሱን ማስተካከል ያስፈልገናል። በተረፈ ግን ተጋጣሚያችን ዛሬ ሙሉ አቅሙን አውጥቶ ነው የተጫወተው። በእኛ በኩል ደግሞ ድክመት ነበረብን። በድክመታችን ላይ መስራት ይገባናል።

ስለተዳከመው የቡድኑ ማጥቃት

በሲዳማ ቡና በኩል መሀል ሜዳ ላይ ያሉ ተጫዋቾች የፈጠራ ክህሎታቸው ከባድ ስለሆነ የእነሱን እንቅስቃሴ በመጀመሪያው አጋማሽ መቆጣጠር አቅቶናል። ሰው በሰውም በዞንም በመሸፈን የእኛ አማካዮች ኳሱን መቆጣጠር አልቻሉም። እነሱን በእንቅስቃሴ ማቆም አልቻሉም። በአጠቃላይ በግልም  ፣ በግሩፕም እንደቡድንም የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ አልነበረም። እንደልብ እንዲጫወቱ ፈቅደንላቸዋል። በአብዛኛው በእኛ ድክመት ላይ የተመሰረተ ነበር።