መረጃዎች | 70ኛ የጨዋታ ቀን

በሳምንቱ መጀመሪያ የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ ቅድመ-መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

ኢትዮጵያ መድን ከአርባምንጭ ከተማ

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከላይ እና ከታች ሦስት ደረጃዎችን ቆጥረን የምናገኛቸው መድን እና አርባምንጭ በሁለት የተለያየ መንገድ ላይ ቢገኙም የደረጃ ዕድገት ለማምጣት የሚያደርጉት የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሪምየር ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውተው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ቀድመው ግብ አስቆጥረው የነጥብ ልዩነቱን የሚያጠቡበትን ሁነት ፈጥረው የነበረ ቢሆንም በዘጠኝ ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦች ተቆጥሮባቸው እጅ ሰጥተው ነጥቡ ከፍ ብሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ጨዋታም ድል ማድረጉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱ ወደ ስምንት ከፍ በማለቱ መድኖች የነገውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ይገባሉ። ጠባብ የተጫዋች ስብስብ ያለው ቡድኑ ጉዳት ፈተናው እየሆነ እያሳሳው ይገኛል። ይህ ቢሆንም ግን በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የማይገኘውን አርባምንጭ ማግኘታቸው ምናልባት የነገውን ፍልሚያ ሊያቀልላቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያሳካው አርባምንጭ ከተማ በተመሳሳይ በሽንፈት ደረጃም አንዴ ቢረታም በቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች የጣላቸው አስር ነጥቦች የሚያስቆጩ ናቸው። ከውጤት ባለፈም ቡድኑ በዘጠና ደቂቃ ውስጥ በወጥነት አለመንቀሳቀሱ አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪን የሚያሳስብ ነው። በአብዛኞቹ ጨዋታዎችም እየመራ ግቦችን እያስተናገደ ውጤቱ ከእጁ ወጣ እንጂ ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ በላይ ይገኝ ነበር። የሆነው ሆኖ በወራጅ ቀጠናው ፉክክር ነጥቦች እየሰፉ ከመሄዳቸው በፊት በቡድን መከላከል እና ማጥቃት ሲንቀሳቀስ የሚታየው አርባምንጭ በቶሎ አሸናፊነትን ማዘውተር ይገባዋል።

በኢትዮጵያ መድን ቤት ኪቲካ ጅማ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን ከእሱ በተጨማሪ አብዱልከሪም መሀመድ እና አሸብር በተመሳሳይ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ እንደሚያመልጣቸው ተገልጿል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዘንድሮ ግንኙነታቸው በፊት በሊጉ በተጋናኙባቸው አራት አጋጣሚዎች በአስገራሚ ሁኔታ አራቱንም አቻ ሲለያዩ ሦስቱ ጨዋታዎች ደግሞ ያለ ግብ የተጠናቀቁ ነበሩ። ዘንድሮ ግን ኢትዮጵያ መድን ሰባት ግቦች በተቆጠሩበት ፍልሚያ አራት ለሦስት አሸንፏል።

አባይነህ ሙላት ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ሲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው ሙሉቀን ያረጋል በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጉን በአራተኛ ዳኝነት ይመራዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከለገጣፎ ለገዳዲ

ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ከድል ጋር የታረቁትን ድሬዳዋ ከተማዎች በሊጉ ግሮጌ ከሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ጋር የሚያገናኘው ፍልሚያ ምሽት 12 ሰዓት ይከናወናል።

አስራ ሁለት ነጥቦችን በተከታታይ ከጣሉ በኋላ ከሲዳማ ቡና ሦስት ነጥብ እና ጎል ያገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁን ላይ በ21 ነጥብ በሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህ ውጤት በክለቡ ዙርያ ያለውን የውጥረት ስሜት በማለዘብ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ከውጤት ማጣት እንዲሁም የቡድኑን ስብስብ እያስተዳደሩበት ባለው መንገድ ዙርያ በብዙሃኑ የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ትችቶች እያስተናገዱ የሚገኝ የነበረ ሲሆን አሁን ከመቀመጫ ከተማው ውጪ የሚያደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ በመርታት የክለቡን ደጋፊ ልብ መልሰው ለማግኘት እንደሚጥሩ ይታመናል።

አሁንም በ6 ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በስብስብ ረገድ በሁለተኛው ዙር ተለውጠው ቢቀርቡም ሁለተኛው ዙርን በሀዋሳ ከተማ 1-0 ሽንፈትን በማስተናገድ ነበር የጀመሩት። በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ያስፈረሟቸውን ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን በሙሉ ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ የተጠቀሙት አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድናቸው በሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ግን ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። ከወዲሁ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሲዳማ ቡና ጋር በ13 ነጥብ አንሰው የተጠቀመጡት ለገጣፎዎች ሳይረፍድ ከወዲሁ በፍጥነት ነጥብ ወደ መሰብሰብ መመለስ ይገባቸዋል።

\"\"

ድሬዳዋ ከተማዎች በነገው ጨዋታ በሙሉ ስብስባቸው የሚቀርቡ ሲሆን በአንፃሩ ለገጣፎ ለገዳዲዎች የዘነበ ከድርን ግልጋሎት ማግኘታቸውን ከመጠራጠራቸው ውጪ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለባቸውም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ያደረጉት መርሃግብር በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች አንድ አቻ በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ተከተል ተሾመ ሲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን የመምራት ዕድል ያገኘው አብዱ ዓሊ ረዳቶች እንዲሁም በተመሳሳይ ሶሬሳ ካሚል ከከፍተኛ ሊጉ አድጎ ለመጀመሪያ ጊዜ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ለጨዋታው ተመድቧል።