ሦስት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ነገ ወደ ዩጋንዳ ያመራሉ

የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎችን ለመምራት ሦስት ዕንስት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ነገ ወደ ዩጋንዳ ያመራሉ።

የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ ይደረጋል። በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች በዞን ደረጃ የሚደረጉ ሲሆን ከፊታችን ቅዳሜ ነሀሴ 5 ጀምሮ የሴካፋ ዞን የቶርናመንት ጨዋታዎች በዩጋንዳዋ ጂንጃ ከተማ ይከናወናል። በውድድሩ ላይ በክለብ ደረጃ የወቅቱ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሦስተኛ ጊዜ በመድረኩ የሚሳተፍ ሲሆን ከባንክ በተጨማሪ በመድረኩ ሦስት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች እንዲዳኙ ስለ መመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ጠቁሟል።

በያዝነው ዓመት የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅን ያገኘችው እና ከሰሞኑ በካይሮ ሲሰጥ በነበረው ስልጠና ከኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ጋር ተከታትላ የተመለሰችው ሲሳይ ራያ እና ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ በታንዛኒያ ቆይታ የነበራት ፀሀይነሽ አበበ በዋና ዳኝነት እንዲመሩ ሲመረጡ በሴካፋ ዞን ውድድሮች በተደጋጋሚ ስትዳኝ የምናውቃት በተጨማሪም በቀጣዩ ዓመት በኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ላይ እንደምታድግ የምትጠበቀው ወይንሸት አበራ በረዳት ዳኝነት ተመርጣለች ፤ ሦስቱም ዳኞች ነገ አመሻሹን ወደ ስፍራው ያመራሉ።

ከሦስቱ ዳኞች በተጨማሪ ተስፋነሽ ወረታው የውድድሩ ኮሚቴ ሆና በመመረጧ በአንፃሩ ሳራ ሰይድ በጨዋታ ኮሚሽነርነት በመጠራቷ በተመሳሳይ ወደ ስፍራው ይጓዛሉ።