ጌታነህ ከበደ ፋሲል ከነማን ተቀላቀለ

ከሲዳማ ቡና ጋር ተስማምቶ እንደነበር ተገልፆ የነበረው ጌታነህ ከበደ ወደ ፋሲል ከነማ ሊያመራ እንደሚችል ተከታታይ ዘገባ አቅርበን በነበረው መሠረት ተጫዋቹ ወደ ዐፄዎቹ አምርቷል።

ከሰሞኑን የዝውውር መስኮቱ መነጋገሪያ የነበረው የጌታነህ ከበደ ጉዳይን በተመለከተ ሶከር ኢትዮጵያ ተከታታይ መረጃዎችን ስታጋራ የነበረ ሲሆን ተጫዋቹ ከሲዳማ ቡና አመራሮች ጋር ተስማምቶ ወደ ክለቡ ለማምራት ከጫፍ እንደደረሰ አስነብበን ነበር። ያለፉትን ሦስት ቀናት ግን የተጫዋቹ የዝውውር መልክ ሌላ ገፅ ይዞ ተጫዋቹ ከፋሲል ከነማ ጋር ድርድሮችን እንዳደረገና ተጫዋቹ መዳረሻው የዐፄዎቹ ቤት ሊሆን እንደሚችል አመላክተን ነበር። አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባረጋገጠችው መሠረት ተጫዋቹ በይፋ ለፋሲል ከነማ ፊርማውን አኑሯል።

በአሁኑ ሰዓት ጌታነህ ከበደ እና ወኪሉ እንዲሁም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚገኙ ሲሆን ተጫዋቹም ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በክለቡ ለመጫወት በይፋ ስምምነቱን አፅንቷል።

ጌታነህ ከበደ እና የፋሲል ከነማ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በብሔራዊ ቡድን አለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን ሁለቱ ግለሰቦች በፋሲል ከነማ አብረው ለመስራት መስማማታቸው የዝውውሩ ሳቢ ጉዳይ ሆኗል።