ባንክ ጋናዊ ተጫዋች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

በዝውውር መስኮቱ በንቃት ተሳትፎ ያደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋናዊ ተጫዋች አምጥቷል።

በአሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ በተመለሱበት የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን እንዳስፈረሙ ይታወቃል። በይፋ ካስፈረሟቸው ተጫዋቾች ውጪ በኢትዮጵያ መድን ያሳለፉትን ባሲሩ ዑመር እና ሲሞን ፒተርን ወደ ቡድናቸው ለመቀላቀል ተስማምተው የነበረ መሆኑን ከቀናት በፊት ዘግበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ቅድመ ስምምነት ፈፅመው የነበሩትን ሦስተኛ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ተጫዋች ማስመጣታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ጋናዊው ካሌብ አማንክዋህ ነው። በመሐል ተከላካይ እና የመስመር ተከላካይ እንዲሁም የተከላካይ አማካይ ሚና መጫወት የሚችለው የ25 ዓመቱ ተጫዋች የእግርኳስ ህይወቱን በሀገሩ ጋና ዌስት አፍሪካ ፉትቦል አካዳሚ (WAFA)፣ አዱዋና ስታርስ እና ኧርትስ ኦፍ ኦክ አሳልፎ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርገውን ዝውውር ለማገባደድ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በይፋ ለክለቡ ፊርማውን ያኖራል።