ንግድ ባንክ የአሠልጣኙን ውል አድሷል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉት አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በክለቡ የሚቆዩበትን ዓመት አራዝመዋል።

በ2016 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከምንመለከታቸው ክለቦች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ይታወቃል። ክለቡ ባለንበት ሳምንት መጀመሪያ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን የአሠልጣኙ በፀሎት ልዑልሰገድን ውል ማራዘሙም ታውቋል።

አሠልጣኝ በፀሎት በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ክለቡን ተረክበው የተሳካ ጊዜን በማሳለፍ ክለቡን ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን ያሳደጉት ሲሆን በቀጣይ ዓመትም ተጠናክሮ ለመቅረብ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው እየቀላቀሉ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ እሳቸው በክለቡ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት የሚቆዩበትን ውል በፌዴሬሽን ተገኝተው መፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።