አዳማ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ሲቀላቅል የአማካዩን ውል አድሷል

አዳማ ከተማ የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅሙ የተከላካይ አማካዩን ኮንትራት አራዝሟል።

በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ወደ ዝውውሩ ከገቡ በኋላ መላኩ ኤልያስ ፣ አሸናፊ ኤልያስ ፣ ሱራፌል ዐወል እና ፍቅሩ አለማየሁን የግላቸው ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአንድ ተጫዋች ውልም አራዝመዋል።

ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ወደ አዳማ አምርቷል። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ አትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና የግብ ዘብ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በመቻል ካሳለፈ በኋላ ቀጣዩ መዳረሻው አዳማ ሆኗል።

ሌላኛው የክለቡ አዲሱ ተጫዋች ኤፍሬም ዘካሪያስ ነው። ከዚህ ቀደም በአዳማ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው እና የኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ስድስተኛው የአዳማ ፈራሚ ሆኗል።

ከሁለቱ አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ ክለቡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ድሬዳዋ ተጫውቶ ባለፈው ዓመት ክለቡን የተቀላቀለውን የተከላካይ አማካዩ ዳንኤል ደምሱን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።