መቻል የግብ ዘብ አስፈርሟል

በአዲስ አሠልጣኝ ቀጣዩን የውድድር ዘመን የሚከውኑት መቻሎች በዝውውር መስኮቱ የመጀመሪያ ተጫዋቻቸውን አስፈርመዋል።

ከሳምንታት በፊት ገብረክርስቶስ ቢራራን የክለቡ አሠልጣኝ አድርጎ የሾመው መቻል ወደ ዝውውር መስኮቱ ጎራ በማለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከማስፈረሙ በፊት የነባሮቹን ምንተስኖት አዳነ እና በኃይሉ ግርማን ውል ማደሱ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ የመጀመሪያ አዲስ ተጫዋቹን ከዩጋንዳ ማስመጣቱን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

መቻልን የተቀላቀለው ግብ ጠባቂው ናፊያን አልዮንዚ ነው። በሀገሩ ዩጋንዳ ተስፋ የተጣለበት የግብ ዘብ እንደሆነ የሚነገርለት አልዮንዚ ያለፉትን ሰባት ዓመታት በዩጋንዳ ሬቨንዩ አውቶሪቲ (URA FC) ሲጫወት አሳልፏል። ዓምና በተደረገው የቻን ውድድር ላይ ለሀገሩ ሦስት ጨዋታዎችን ያደረገው ተጫዋቹም በአንድ ዓመት ውል ወደ መቻል ተዘዋውሯል።