ከፍተኛ ሊግ | ቤንች ማጂ ቡና በርካታ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ የሚሳተፈው ቤንች ማጂ ቡና የ14 ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የነባሮችን ውልም አራዝሟል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ በተጠናቀቀው ዓመት በምድብ ሀ ስር ተደልድሎ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ከጫፍ ደርሶ በንግድ ባንክ በመበለጡ ሳይሳካለት ቀርቶ የነበረው ቤንች ማጂ ቡና በዘንድሮው የሊጉ ተሳትፎው በምድብ ሀ ስር የተደለደለ ሲሆን የአምናውን ጥንካሬ ለማስቀጠል በማሰብ በአሰልጣኝ መሐመድ ኑርንማ መሪነት 14 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን የ11 ነባሮችን ውል ደግሞ ስለማደሱ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል።

ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ስንመለከት በግብ ጠባቂ ቦታ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና በተጠናቀቀው ዓመት በኢትዮ ኤሌክትሪክ የነበረው ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለ ፣ ናትናኤል ተፈራን ከአዲስ ከተማ ፣ ዳንኤል ይስሀቅን ከመድን ፣ በተከላካይ ቦታ ላይ ዮሐንስ ተስፋዬ ከአርባምንጭ ከተማ ፣ አብዱል ሀሚድ ከአዲስ ከተማ ፣ አብዱልአዚዝ አማን ከባቱ ፣ አብዲ ራህመቶ ከስልጤ ወራቤ ፣ በአማካይ ስፍራ ላይ ተስፋዬ በቀለ ከባቱ ፣ ከማል ሀጂን ከአዲስ አበባ ከተማ ፣ ጃፋር ሙደሲር ከስልጤ ወራቤ ፣ ሳላሀዲን ሙሰማ ከባቱ ፣ በአጥቂ ቦታ የቀድሞውም የሰበታ ከተማ እና ኤሌክትሪክ ተጫዋች ኢብራሂም ከድር ፣ ዳግም ሠለሞን ከመድን እና አጥቂው ወንድማገኝ ኪራ በአርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ካሳለፈ በኋላ ወደ ቀደመ ክለቡ በድጋሚ ተመልሷል።

ቡድኑ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ በክለቡ የነበሩትን ጌታሁን ገላዬ ፣ ብሩክ ወንዱ ፣ ሥንታየሁ ሠለሞን ፣ በእውቀቱ ማሞ ፣ ጥዑመልሳን ኃይለማሪያም ፣ አንዱዓለም ድክሬ ፣ ዳንኤል አገኘው ፣ ልጅዓለም ተሰማ ፣ ሀሰን ሁሴን ፣ ዘላለም በየነ እና ያሬድ ወንድማገኝን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሞላቸዋል።