መረጃዎች| 18ኛ የጨዋታ ቀን

ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የጀመረው አምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገም ይቀጥላል። ነገ የሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።    

አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሁለት ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ የሚገቡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የነገው ቀዳሚ ፍልሚያ ይሆናል።

ከአራት ጨዋታዎች በአንዱ ድል አድርገው በሦስት ጨዋታ አቻ በመለያየት ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት አዳማዎች በውድድር ዓመቱ ሽንፈት አልቀመሱም።
ይህ ክብረ ወሰንም በሊጉ ሽንፈት ካልቀመሱ አምስት ክለቦች ተርታ አሰልፏቸዋል። አዳማዎች በመጨረሻው ሳምንት ከሊጉ መሪ አቻ ተለያይተው ነጥባቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል። በጨዋታው ምንም እንኳን የትኩረት ችግር ተስተውሎባቸው በእጃቸውም የገባው ነጥብ አሳልፈው ቢሰጡም ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የነበረውን ውስን ክፍተቶች ላይ መሻሻሎች አሳይቷል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በአማካይ ክፍላቸው ላይ ውስን ለውጦች ካደረጉ በኋላ በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ የሚታይ ለውጥ አምጥተዋል። በነገው ጨዋታም የአጨዋወትም ሆነ ቋሚ አሰላለፍ ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም በሁለት ጨዋታዎች ላይ ግቡን ሳያስደፍር ከወጣ በኋላ ባለፈው ጨዋታ የትኩረት ችግሮች የተስተዋሉበት የተከላካይ ክፍላቸው ወደ ቀደመው ብቃቱ የመመለስ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

ከአራት ጨዋታዎች አንድ ድል፣ አንድ አቻና ሁለት ሽንፈት የገጠመባቸው ብርቱካናማዎቹ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ አዳማን ይገጥማሉ። ድሬዳዋዎች በመጀመርያው ሳምንት ሀምበሪቾን ካሸነፉ በኋላ ድል ተራርቀዋል። በአብዛኛው በመስመሮች አልፎ አልፎም በረዣዥም ኳሶች ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ያስመለከቱን አሰልጣኝ አስራት አባተ ምንም እንኳ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ በንግድ ባንክ ሽንፈት ቢያስተናግዱም ለሁለት ጨዋታዎች ከግብ ጋር ተኳርፎ የነበረው ቡድናቸው ወደ ግብ ማስቆጠር ተመልሷል። በነገው ጨዋታም ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለውን አጨዋወት ላይ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ግብ አስቆጥሮ የመውጣቱ መነሻም ከላይ የተጠቀሰው የሚፈጠሩት ዕድሎች በቁጥርም በጥራትም ማነስ ነው። በጉዳት ላይ የቆየው አጥቂው ተመስገን ደረስ ከጉዳት መመለሱም የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግር በመጠኑ እንዲቀርፉ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል።

ብርቱካናማዎቹ የያሲን ጀማል እና መሐመድ አብዱልፈታህ ግልጋሎት አያገኙም ፤ በጉዳት ላይ የነበረው ተመስገን ደረስ አገግሞ ወደ ሜዳ መመለሱ ደግሞ ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።

ክለቦቹ በሊጉ ታሪካቸው 22 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 11 ጨዋታ በድል ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ 6 አሸንፏል። ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። አዳማ 25 ፣ ድሬዳዋ 18 ጎሎችንም በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።

መቻል ከ ሀምበሪቾ

ወደ ሰንጠርዡ አናት ለመጠጋት እና ከግርጌው ለመላቀቅ የሚጫወቱት ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት 12:00 ይከናወናል።

ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ድል፣ አንድ ሽንፈትና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት መቻሎች
የሰበሰቧቸውን ሰባት ነጥቦች ከፍ አድርገው ወደ ሊጉ አናት ለመጠጋት ሀምበሪቾን ይገጥማሉ። ቡድኑ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ጠንካራውንና ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደውን ወላይታ ድቻን ማሸነፉ በጥሩ የሥነ ልቦና ደረጃ ወደዚህ ጨዋታ እንዲገባ ይረዳዋል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም በጨዋታው ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንካሬውን እያጣ የሚገኘው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ለውጦች ማድረግ የግድ ይላቸዋል። በወላይታ ድቻው ጨዋታም የተጠቀሰው ችግር በስፋት ተስተውሏል። ሆኖም እስከ ሦስተኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር መውጣት አቅቶት የነበረውና አምስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው በመጠኑም ቢሆን መሻሻሎች አሳይቷል። በጠንካራው ጨዋታም በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ሳያስተግድ ወጥቷል። በነገው ጨዋታም ይህንን ጥንካሬያቸው ማስቀጠል በዋነኝነት ደግሞ የቡድኑ የፈጠራ አቅም ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሀምበሪቾዎች ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት አቻና ሁለት ሽንፈት አስተናግደው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ በተከታታይ የአቻ ውጤት አስመዝግቦ ከቀደሙት ውጤቶቹ አንፃር መሻሻሎች አሳይቷል። ሆኖም በእንቅስቃሴ ረገድ ሊጉን በጀመረበት ቅኝት መቀጠል አልቻለም። በተለይም አቻ በተለያዩበት የመጨረሻው ጨዋታ በእንቅስቃሴም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ተዳክመው ታይተዋል። በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያመረተው የቡድን የማጥቃት አጨዋወት በተጠቀሰው ጨዋታ ላይ ግን በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ወጥቷል። ካላቸው ስብስብ አንፃር ጥሩ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ ከነገው ተጋጣምያቸው ጥንካሬ አንፃር በአጨዋወታቸው ላይ ውስን ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል። በተለይም በየጨዋታው በአማካይ 1.5 ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ ተከላካይ ክፍልና በመጨረሻው ጨዋታ የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገረው የአማካይ ክፍላቸው መጠነኛ ጥገና ይሻል።

በመቻል በኩል አስቻለው ታመነ እና ግሩም ሀጎስ ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን ተስፋዬ አለባቸውም መጠነኛ ጉዳት አስተናግዷል። በረጅም ጊዜ ጉዳት ከቡደኑ የራቀው እና በቅርቡ ልምምድ የጀመረው ፍፁም ዓለሙም ሊጉ ከአንድ ወር በኋላ ሲመለስ ለጨዋታ ዝግጁ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሀምበሪቾዎች አሁንም የኤፍሬም ዘካርያስ ግልጋሎት አያገኙም።