የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 ወልቂጤ ከተማ

“ቡድናችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ጥሩ ሂደት ነው ብዬ አስባለሁ” አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ


“ትልቁ ችግራችን እኛ ላይ በመጀመሪያ ደቂቃ የሚቆጠሩብን ግቦች ናቸው” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት

በምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች ወልቂጤ ከተማን 2ለ0 ካሸነፈበት መርሀግብር ፍፃሜ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስን አድርገዋል።

አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በተከታታይ ድል የሊጉ መሪ መሆን ስለመቻላቸው እና ስለ ዛሬው ጨዋታ…

“ወልቂጤ ከተማ ያለፉትን ጨዋታዎች ምን አይነት ጨዋታ ይጫወታል የሚለውን በደንብ አይተናቸው ነበር እና ወልቂጤ ምንም ነጥብ ባያገኙም ኳስ ከሚጫወቱ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። ይህንን ጨዋታ ደግሞ በጥንቃቄ መጫወት ነው ያለብን ፣ ከጨዋታው በፊት ተነጋግረን ነበር የመጣነው ዝግጅታችንም በኳስ ቁጥጥርም እንደዚውም ጎል በማግባት ሜዳ ላይ በሚያጋጥሙ ነገሮች በሙሉ የተሻለ ስለ መሆን አስበን መጣን ፣ የመጀመሪያ ሀያ እና አስራ አምስት ደቂቃ ላይ በደንብ ተጭነን በኳስ ቁጥጥርም የተሻለ ሆነን በሀያ ደቂቃ ውስጥ አንድ አራት የሚሆኑ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለን ነበር ፣ ከዚህም ውስጥ አንዱ ጎል መሆን ችሏል። ይሄ አጀማመራችን ደግሞ የበለጠ ወደ ሪትም እንድንገባ እና የተሻለ አርባ አምስት እንድናሳልፍ ትልቁን በር ከፍቶልናል ብዬ አስባለሁ።”

በቀጣይ የሚኖረው የአንድ ወር ዕረፍት አሁን ያለውን የቡድኑን መነቃቃት ያቀዘቅዛል ወይስ እንደ በጎ አጋጣሚ ይጠቅማል…

“እንግዲህ ዕረፍት ሁለት ነገር ነው ያለው። አንድ ኔጌቲቭ ፓርት አንዳንድ ጊዜ ቡድን የሚያወርድ ባህሪ ይኖረዋል ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቡድንን ማስተካከያ መድረክም ሆኖ ያገለግላል። ለምሳሌ ቡድንህ ሊወርድ የሚችለው በምንድነው የጨዋታ ሙድ ውስጥ እየገባን ፣ አዲስ እንደ መሆናችን ከጨዋታ ጨዋታ እየተስተካከልክ ይሄንን የማስቀጠልን ነገር ስታስብ ፣ ከጨዋታ መራቅ በጥንቃቄ ማየት የሚገባን ነገር ነው ብዬ አስባለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ያሉብህን ድክመቶች ፣ ጉዳቶች ቢኖሩብህ ሁለት ጉዳቶች በፊትም የተመዘገቡ ጉዳቶች ነበሩ ዛሬ በጨዋታው ላይም ሁለት ጉዳት አጋጥሟል እና እነኚህን በሌላ መልኩ ስታየው ተጫዋቾቻችን ማገገሚያ አድርገው በመሉ ሀይል የምንመጣበትን አጋጣሚ እንፈጥራለን ፣ ስለዚህ ዞሮ ዞሮ ዕረፍቱ ጉድለታችንን የምናስተካክልበት ፣ ከጨዋታ ሪትምም እንዳንወጣ ስራዎችን እየሰራን ቆይተን ለመመለስ ነው ጥረት የምናደርገው።”

ስላለፉት አምስት የጨዋታ ሳምንታት…

“ከሞላ ጎደል ወጣ ገባዎች ቢኖሩትም ፣ በጠበቅነው ልክ ነው ብዬ አስባለሁ ፣ ማለት የመጀመሪያዎች አካባቢ ቡድናችን በትክክል ያለ መስተካከል ነበረበት ግን ቀስ እያለ ደግሞ የመስተካከል ቅርፁንም የመያዝ ነገር አለው እና ባሰብነው ልክ ቡድናችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ጥሩ ሂደት ነው ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። እንደተነጋገርነው እነርሱም ተጭነው ለመጫወት ሞክረው ነበር ፣ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ሀያ ደቂቃዎች ውስጥ ትልቅ ክትትል አድርገን ነበር አጋጣሚ ሆኖ ጎል ተቆጥሮብናል። ከዕረፍት በኋላ ደግሞ የተሻለ እንቅስቃሴ እና ወደ ትክክለኛ ቦታችን ለመመለስ ያደረግናቸው ነገሮች ጥሩ ስለነበሩ ፣ ለማግባት ተጫዋቾቹም ያደረጉት ነገር በአጠቃላይ በጣም ደስ የሚል ነበር በአጠቃላይ ግን የእኛ ቡድን ይሻላል ብዬ ነው የማስበው።”

በመጀመሪያ ሀያ ደቂቃዎች ስለ ተደረጉ ሁለት ቅያሪዎች…

“አዳምስ ረጅም ጊዜ ከእኛ ጋር አልነበረም ፣ ከእኛ ጋር ለመላመድ እርሱንም ቼክ ለማድረግ ነበረ ፣ መጨረሻ ላይ ግን ሜዳ ላይ የታየው ነገር እኛ እንደፈለግነው ሳይሆን መስራት እንደሚጠበቅበት ነበር ፣ መሐመድም እንደዛው እርሱም የመጀመሪያ ጨዋታው ስለነበረ ትንሽ የመረበሽ ነገሮች ካልሆነ በቀር ለቀጣዩ ጨዋታዎች በዕረፍት ጊዜያችን ግን አስተካክለን እንመጣለን።”

ከአራተኛው ሳምንት አንፃር ስለ ተደረጉ በርከት ያሉ የተጫዋች ቅያሪዎች…

“ብዙ ለውጦች ነበሩ። ሁሉም መጫወት ስለሚችሉ ጨዋታው ተደጋጋሚ ስለሆነ እያሳረፍን እየቀያየርን ለመጫወት ስላሰብን ነበር።”

በቀላሉ ጎል የሚቆጠርበት በዛው መጠን ግብ ያለ ማስቆጠር ችግር በቡድኑ ላይ ስለ መኖሩ…

“ትልቁ ችግራችን እኛ ላይ በመጀመሪያ ደቂቃ የሚቆጠሩብን ግቦች ናቸው ትልቅ ችግር እየሆነብን ያለው ፣ ሁለተኛ ደግሞ ለማግባት ትንሽ እየተቸገርን ነው በታቸለ አቅም ያሉንን ተጫዋቾች ይዘን ለመስራት እንሞክራለን። ሌላ የውጪ ዜጋ ተጫዋችም አለ እርሱ እስኪመጣልን ባሉ ተጫዋቾች እንሰራለን በዚህ ላይ ተዘጋጅተን ወደ ጨዋታ እንመለሳለን።”