ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲሞን ፒተር እና ኪቲካ ጅማ ግቦች ወልቂጤ ከተማን 2-0 መርታት ችሏል።

በምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወልቂጤ ከተማ ሲገናኙ ኢትዮጰያ ንግድ ባንኮች በድሬዳዋ ላይ ድል የተቀዳጀውን ስብስብ ሳይለውጥ ዛሬም ወደ ሜዳ ሲገባ በወልቂጤ በኩል በባህርዳር ከተረታው ቡድናቸው የስድስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። ተስፋዬ መላኩ ፣ ሔኖክ ኢሳያስ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ስንታየሁ መንግስቱ በአዳነ በላይነህ ፣ ዋሀቡ አዳምስ ፣ ተመስገን በጅሮንድ ፣ መሐመድ ናስር ፣ ዳንኤል ደምሴ እና አብርሀም ኃይሌ ተተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች በሚያደርጉት ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ጨዋታው ለተመልካች እጅግ ማራኪ የነበረ ሲሆን ባንኮቹ ገና በ 2ኛው ደቂቃ የሠራተኞቹን ሳጥን ፈትነው ተመልሰዋል። ብሩክ እንዳለ የሰነጠቀለትን ኳስ ወደ ቀኙ የሳጥኑ ክፍል ሮጦ በመግባት የተቆጣጠረው ሱሌይማን ሐሚድ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጥሩ የኳስ ቅብብል ለማድረግ ቢሞክሩም የንግድ ባንኮችን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የተቸገሩት ወልቂጤዎች 12ኛው ደቂቃ ላይ በሠሩት ስህተት ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። ዋሃብ አዳምስ  ለማቀበል ሲሞክር በሠራው ስህተት አቋርጦ ኳሱን ያገኘው አዲስ ግደይ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ለሲሞን ፒተር አመቻችቶ ቢያቀብልም ሲሞን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ጨዋታው 13ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከአንድ ደቂቃ በፊት ወርቃማ ዕድል ያመከነው ሲሞን ፒተር በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን መሪ በማድረግ ክሷል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ሲታትሩ የነበሩት ባንኮቹ 20ኛው ደቂቃ ላይም ንጹህ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ኪቲካ ጅማ በግሩም ዕይታ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሱሌይማን ሐሚድ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመግባት ያልተቸገሩት ንግድ ባንኮች በሚያደርጉት ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ታጅበው 23ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ኪቲካ ጅማ ከመሃል ሜዳ ኳስ ይዞ ሾልኮ በመውጣት እየገፋ የወሰደውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ የሠራተኞቹ መረብ ላይ አሳርፎት የቡድኑን መሪነት አጠናክሯል።

ጨዋታውን ማድረግ ከመጀመራቸው በፊት በውዝግብ የተሞላ የዝግጅት ጊዜ እንዳሳለፉ የተነገረላቸው ወልቂጤ ከተማዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ እና ተስፋየ መላኩን ቀይረው በማስገባት ሁለቱንም ሳጥኖች ለማጠናከር ጥረት ቢያደርጉም ካደረጓቸው ጥቂት የማጥቃት እንቅስቃሴ ሙከራዎች ውጪ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአጋማሹ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎችም ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሠራተኞቹ መጠነኛ መሻሻል በማሳየት የወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲያስመልሱ ንግድ ባንኮች በአንጻሩ ከነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ግለት በመብረድ እና የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ በተመሳሳይ ሰዓት በማድረግ ጨዋታውን በማረጋጋት ውጤቱን ይዘው ለመውጣት ፍላጎት አሳይተዋል።

በአጋማሹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ወልቂጤዎች ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ 74ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ባሻገረው እና ተስፋየ መላኩ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ አግዳሚ ለጥቂት በወጣበት ኳስ 82ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተመስገን በጅሮንድ ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት መሬት ለመሬት መትቶት ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በመለሰበት ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው እንቅስቃሴውን በሚፈልጉት ሂደት ባስቀጠሉት ንግድ ባንኮች 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።