የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-0 ሻሸመኔ ከተማ

“ብዙም ዕድል መፍጠር አልቻልንም” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ


“ወደ ጎል ብዙም አልሄድንም ፣ ሁለታችንም ተከላክለን ነው የወጣነው” ጊዜያዊ አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ

ሻሸመኔ ከተማ የሊጉን የመጀመሪያ ነጥብ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለ ጎል ተለያይቶ ካሳካበት ጨዋታ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታን አድርጋለች።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – ሀድያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው…

“መከላከል ላይ ጥሩ ስራ እየሠራን ማጥቃት ላይ ማስቆጠር አቅቶናል። የምናገኛቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም ፣ ስለዚህ ማጥቃቱ ላይ ደግሞ በዚህች ባለችን ጊዜ መሥራት የሚገባንን ሠርተን በማጥቃቱ ላይ እንመጣለን ብዬ ነው የማስበው። ሌላው እንዳለ ነው በረኛ ምንም ሳይዝ ይወጣል ግን የምናገኘውንም አልተጠቀምንም ፣ ብዙም ዕድል መፍጠር አልቻልንም ያገኘነውንም አልተጠቀምንም።”

በአራት ጨዋታዎች ላይ አንድም ግብ አለማስቆጠራቸው ፣ ቡድኑ ስላጣው ነገር እና ስለ አማካዮች…

“ማጥቃት እና ጎል መጨረስ ነው ያልቻልነው። የተገኙትን አልጨረስንም ሦስትም ይገኝ አራትም ይሁን ሁለትም እነርሱን እኮ መጨረስ አለብህ መጀመሪያ ፣ ስለዚህ የምናገኛቸውን መሐል ሜዳ ላይ ያሉ ተጫዋቾች ብዙ ዕድል ፈጥረዋል? አልፈጠሩም! ነገር ግን ያገኘነውን ጨርሰናል? አልጨረስንም። የተገኘውን ካልጨረስክ የመሐል ሜዳው ሁለተኛ ችግር ነው። ብትጨርስ እኮ አንድም ቢሆን አንድ ለዜሮ ማሸነፍ በቂ ነው። የመሐል ሜዳዎቹ ደግሞ ምንም ዕድል ለአጥቂዎቹ አልፈጠሩም ማለት እንችላለን።”

ከዚህ በፊት የግብ ዕድሎች ቡድኑ ይፈጥር ነበር ዛሬ ግን ሁለት ብቻ ስለመሆናቸው …

“ጨዋታዎች እየበዙ ሲመጡ ፣ ጎልም ባላገባህ ቁጥር የምትጫወተው ጨዋታ ተረጋግተህ አይሆንም። ተረጋግተህ ካልተጫወትክ ደግሞ አዕምሮ ወሳኝ ነው ፣ ያለ አዕምሮ እግር ኳስ መጫወት አትችልም። በአዕምሮ ተረጋግተህ መጫወት መቻል አለብህ እና ይሄ ጎል አለማግባታችን እንዳንነቃቃ አድርጎናል ስለዚህ የምናገኛቸውን አልጨረስናቸውም ብዙም ባይሆን።”

ጊዜያዊ አሰልጣኝ በቀለ ቡሎ – ሻሸመኔ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“በጣም ጥሩ ነው የተመጣጠነ ጨዋታ ነው። ብዙ ሙከራ እኛም ጋር እነርሱም ጋር የለም ወደ ጎል ብዙም አልሄድንም ፣ ሁለታችንም ተከላክለን ነው የወጣነው ብዬ የማስበው ጥሩ ነው እንደ መጀመሪያ ውጤት በጣም ነው የኮራውበት ደስ ብሎኛል ፣ የተጠማነውን ውጤት ቢያንስ ይቺ አንድ ነጥብ ቢያንስ ማገገሚያ ትሆናለች ብዬ አስባለሁ።”

በጨዋታው የግብ ዕድልን አለመፍጠራቸው …

“ለወደፊት እየተቀረፈ ይሄዳል ብዬ ነው የማስበው ፣ ምናልባት ከሽንፈት ስለመጣን ተጠንቅቀን ለመጫወት ነው የሞከርነው የራሳችንን ቤት ሸፍነን ወደ ሰው ቤት የምንሄደው ብለን ነው የእኛን ቤት ያስከበርነው ፣ ምክንያቱም ከተቆጠረብህ ወደ ጎል ፍለጋ ከምትሄድ የራስህን ቤት ሸፍነህ ወደ ሰው ቤት መሄድ አለብህ ብዬ ነው የማምነው።”

በቀጣይ በሚኖረው ዕረፍት ለመስራት ስለታሰቡ ጉዳዮች…

“በቀጣይ ዕረፍት ነው። በዕረፍቱ መሐል ጥሩ ቡድን ወይንም ጥሩ ግንባታ ለመገንባት ቡድኑን አነሳስተን ጥሩ ልምምድ አሰርተን ከዚህ የተሻለውን ጨዋታ እናደርጋለን ብዬ ነው የማስበው።”