ሪፖርት | እጅግ ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

ሀዲያ ሆሳዕናን ከሻሸመኔ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ተደርጎበት 0-0 ተጠናቋል።

የሳምንቱ የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ሀዲያ ሆሳዕናን ከ ሻሸመኔ ከተማ ሲያገናኝ  ሀዲያዎች ከሀምበሪቾ አቻ ሲለያዩ ሻሸመኔ ደግሞ በሲዳማ ቡና ከተረታው ስብስብ በተመሳሳይ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። በሀዲያ በኩል በረከት ወልደዮሐንስ ፣ ሄኖክ አርፊጮ ፣ ዘካርያስ ፍቅሬ ፣ ተመስገን ብርሀኑ እና ሠመረ ሀፍታይ አርፈው ካሌብ በየነ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ ፣ ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና የኋላሸት ሠለሞን በምትኩ ወደ ሜዳ ሲገቡ በሻሸመኔ በኩል ደግሞ ኬን ሰይዲ ፣ ኤቢሳ ከድር ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ማይክል ኔልሰን እና አብዱልከሪም ቃሲም በአቤል ማሞ ፣ ወጋየሁ ቡርቃ ፣ ጌታአለም ማሙዬ ፣ እዮብ ገብረማርያም እና አሸናፊ ጥሩነህ ተተክተዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችሉም በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገው ነበር። ሆኖም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን እጅግ ደካማ ነበር።

ለተመልካች ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት በቀጠለው ጨዋታ 27ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለን በጉዳት ምክንያት አስወጥተው በስንታየሁ ወለጨ የተኩት ነብሮቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ በሳሙኤል ዮሐንስ ከሳጥን አጠገብ ካደረጉት ሙከራ ውጪ ሁለቱም ቡድኖች አንድም ዒላማውን የጠበቀም ሆነ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ አሰልቺ ሆኖ ሲቀጥል የሀዲያው የመስመር ተከላካይ ካሌብ በየነ 56ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ከወጣበት ሙከራ ውጪ በሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ምንም ግለት ሳይታይበት ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።