መረጃዎች| 16ኛ የጨዋታ ቀን

የአምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ሻሸመኔ ከተማ

ሁለት ከሰንጠረዡ ግርጌ ለመላቀቅ ወደ ሜዳ የሚገቡ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ከአራት ጨዋታዎች ሁለት አቻና ሁለት ሽንፈት አስተናግደው በሁለት ነጥቦች በ14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ሻሸመኔ ከተማን ይገጥማሉ።

በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ከሀምበሪቾ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይተው ወደዚ ጨዋታ የሚቀርቡት ሀድያዎች ባካሄድዋቸው ጨዋታዎች በአብዛኛው በረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም አጨዋወቱ ስኬታማ አድርጓቸዋል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ቡድኑ በአራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ማስቆጠሩ እና ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ አለማስቆጠሩም የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ድክመት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አራት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠጣር የኋላ ክፍል ያለው ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ በማጥቃቱ ላይ ግን አልተሳካላቸውም። በመጨረሻው ጨዋታም በአጥቂ ክፍሉ ላይ ያደረጉት ውስን ለውጥ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘላቸውም፤ ይህንን ተከትሎም ከተከታታይ ጎል አልባ አቻዎች ለመላቀቅ አሁንም ለውጦች ማድረጋቸው አይቀሪ ይመስላል።

በነገው ጨዋታም አሰልጣኝ የቀየረ ከወዲሁ አጨዋወቱ ለመገመት የሚያዳግት ቡድን እንደመግጠማቸው ፈተናው ቀላል ይሆንላቸዋል ተብሎ አይገመትም። በሊጉ ቡድኖች አሰልጣኝ ከቀየሩ በኋላ በመጀመርያ ጨዋታቸው በተለየ ተነሳሽነት ሲገቡ ላስተዋለም ይህንን መገመት አያቸግረውም።

በሊጉ ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት ሻሸመኔዎች ከቀናት በፊት ካደረጉት የአሰልጣኝ ቅያሪ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በጨዋታም በአሰልጣኝ በቀለ ቡሎ እየተመሩ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ በአራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች በማስተናገድ የሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበት ደካማ የመከላከል ክብረ ወሰን ያለው ክለብ ሆኗል። የአዲሱ አሰልጣኝ ቀዳሚ ስራም የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኝ በቀለ በነገው ዕለት የሚከተለውን አጨዋወት ከወዲሁ ለመተንበይ ቢያዳግትም ከነበረው ጥቂት የዝግጅት ግዜ አንፃር በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይከተላል ተብሎ ይታመናል።

በሻሸመኔ ከተማ በኩል ቻላቸው መንበሩ በጉዳት ቡድኑን አያገለግልም። በሀድያ ሆሳዕና በኩል የሳመኤል ዮሐንስ መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ እና ዳግም ንጉሴ በጉዳት በጨዋታው አይሳተፉም።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወልቂጤ ከተማ

በአራተኛው ሳምንት ላይ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፈው ነጥባቸውን ከፍ ያደረጉት ንግድ ባንኮች ግስጋስያቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። እስካሁን ድረስ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሁለት ድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበው ምንም ሽንፈት ያልቀመሱት ባንኮች ሦስት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አላቸው። በሊጉም ከወላይታ ድቻ ቀጥሎ ጥቂት ግቦች የተቆጠረበት ክለብ ሆኗል። በአመዛኙ ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ በፀሎት በመጨረሻው ብርቱካንማዎቹን በገጠሙበት ጨዋታ የግብ ዕድሎች አፈፃፀም ችግሮቻቸው ቢቀርፉም ይህንን በጎ ጎን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኙ ውጤታማ ያደረጋቸው አጨዋወትና ቋሚ አሰላለፍ አስቀጥለው ወደ ጨዋታው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት አቻና ሁለት ሽንፈት አስተናግደው በሁለት ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤዎች ላለፉት ሦስት ቀናት ከልምምድ ርቀው በብዙ ችግሮች ተተብትበው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ወደ ነገው ጨዋታ ይገባሉ።

አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት ኳስን ለመቆጣጠር የሚታትር ቡድን ቢገነባም ቡድኑ ውጤታማነት ረገድ ጥሩ ክብረ ወሰን የለውም። ቡድኑ በአራት ጨዋታ በአማካይ 0.5 ነጥቦችን ይዞ መውጣቱም ለዚህ ማሳያ ነው። ቡድኑ በተለይም ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየት ትልቅ ችግር ይሰተዋልበታል። በአራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ የማስቆጠሩ ምክንያትም ይህ የተጠቀሰው ችግር ነው። አሰልጣኙ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ያለው የአፈፃፀም ችግር ከማስተካከል ባለፈ በመከላከል አደረጃጀቱ ላይም ብዙ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅበታል። ስምንት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ከሌላው የቡድኑ ክፍሎች በበለጠ አንገብጋቢ ጥገና እንደሚያስፈልገውም በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ተስተውሏል።

ንግድ ባንኮች የተከላካዩ ካሌብ አማንክዋህ ግልጋሎት አያገኙም።