ሪፖርት | የሳምንቱ ምርጥ ጨዋታ አቻ ተጠናቋል

ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ቡና እና በወላይታ ድቻ መካከል የተደረገው የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር እጅግ ብርቱ ፉክክር ተደርጎበት 2-2 ተጠናቋል።

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና በፋሲል ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በመቻል ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾችን በማድረግ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል። ቡናማዎቹ ወንድሜነህ ደረጀ እና መስፍን ታፈሰን አሳርፈው በራምኬል ጀምስ እና አማኑኤል አድማሱ ሲተኩ በድቻ በኩል በአንፃሩ አስናቀ አምታታውን በኬኔዲ ከበደ ፣ ባዬ ገዛኸኝን በዘላለም አባተ ለውጠዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ዲቻዎች በአንጻሩ የሚያገኙትን ኳስ ሁሉ ከራሳቸው የግብ ክልል በፍጥነት በማውጣት ተጭነው ለመጫወት ሲታትሩ ታይተዋል። የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ኬኔዲ ከበደ ከቀኝ መስመር አክርሮ ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ሲመለስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ጸጋዬ ብርሃኑ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

ቀስ በቀስ አጨዋወታቸውን ወደ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የቀየሩት ቡናማዎቹ 23ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን አድርገዋል። ብሩክ በየነ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ቢኒያም ገነቱ ሲያቋርጥበት የተመለሰውን ኳስ የሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ወልደአማኑኤል ጌቱ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም አስወጥቶበታል። በሴኮንዶች ልዩነትም አማኑኤል አድማሱ ከሳጥን አጠገብ ያልተጠበቀ ሙከራ አድርጎ የግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ትኩረት ማጣት ተጨምሮበት ግብ ሊሆን ሲል የግቡ አግዳሚ ገጭቶ መልሶበታል።

መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ተጭነው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 38ኛው ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ሹምበዛ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግበትም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ተከላካዩ ዋሳዋ ጄኦፍሪ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ከሳጥን ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ አድርጓል። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ዲቻዎችም ተጨማሪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ለተመልካች እጅግ ማራኪ ፉክክር እየታየበት ሲቀጥል በመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ግብ አስቆጥረዋል። በቅድሚያም 52ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ግርማ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ለመቆጣጠር ሲጣጣር ኳሱን ያገኘው አብነት ደምሴ በቀላሉ ከመስመር በማሳለፍ አስቆጥሮት ወላይታ ድቻን አቻ ሲያደርግ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ አማኑኤል አድማሱ ከሳጥን አጠገብ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት አስደናቂ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጸጋዬ ብርሃኑን አስወጥተው ብሥራት በቀለን በማስገባት የግራውን የማጥቃት መስመራቸውን ያጠናከሩት ወላይታ ድቻዎች ያደረጉት ቅያሪ 73ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል። ብሥራት በቀለ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቢኒያም ፍቅሩ አስቆጥሮት ድቻን በድጋሚ ወደ አቻ መልሷል።

በብርቱ ፉክክር እጅግ እየተጋጋለ በቀጠለው ጨዋታ በሁለቱም በኩል በሚደረገው ዕረፍት የለሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ አጓጊ ሆኖ ሲቀጥል 87ኛው ደቂቃ ላይ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አንተነህ ተፈራ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ብሩክ በየነ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበት አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በሁለቱም በኩል ለተመልካች ማራኪ እንቅስቃሴ የተደረገበት ጨዋታ በመጨረሻም 2-2 ተጠናቋል።