የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-2 ወላይታ ድቻ

“ይህን የእናንተን ትልቅ የበይነ መረብ ሚዲያ ተጠቅሜ ከምንም በላይ ደጋፊዎቻችንን ስለ ባለፈው አስተያየቴ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች


“ለተመልካች ሊያዝናና የሚችል ግሩም እግር ኳስ ነበር” አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ

ሊጉ ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት የመጨረሻ በሆነው የቡናማዎቹ እና የጦና ንቦቹ ጨዋታ አዝናኝ እንቅስቃሴዎችን አስመልቶ 2ለ2 በሆነ ውጤት ከተፈፀመ በኋላ አሰልጣኞች የድህረ ጨዋታ ሀሳባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች – ኢትዮጵያ ቡና

ሁለቴ መርተው ነጥብ ስለመጣላቸው…

“ይህን የእናንተን ትልቅ የበይነ መረብ ሚዲያ ተጠቅሜ ከምንም በላይ ደጋፊዎቻችንን ስለባለፈው አስተያየቴ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ ፤ በተመሳሳይ የክለቡን አመራሮችን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ።ሁሉም የአለም እግር ኳስን የሚከታተል ሰው እንደሚያውቀው በእነ ሪያል ማድሪድ ባየር ሙኒክ እና ሊቨርፑል ባሉ ትላልቅ ክለቦች ውስጥ እንኳን በዋና አሰልጣኙ እና ክለቡን በሚመሩት አካላት መካከል ያለው ግንኙነት አለ ለማለት በሚያስቸግር መልኩ በችግሮች የተሞላ ቢሆንም አሰልጣኞቹ ግን የክለቡን የውስጥ ጉዳዮች በሚመለከቱ ጉዳዮች በአደባባይ ሀሳብ ሲሰጡ አንመለከትም። ስለዚህ እኔም ይህን በማድረጌ በተለይ በተለይ ደጋፊዎቻችንን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ከሰጠሁት አስተያየት በኃላ የማይገባኝን ክብር የሰጠኝ የክለቡ ደጋፊ ላይ ያየሁት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስለሆነ በድጋሚ ይቅርታ ማለት እፈልጋለሁ።

“70% በሚሆነው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የሚባል የጨዋታ ቁጥጥር ነበረን ፣ በእቅዳች መሰረት በእኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ጋብዘናቸው በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም አስበን ነበር። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ነገሮችን ለወጥ አድርገን 10 ሰው ወደ እነሱ ሜዳ በማስገባት ተጭነን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። በጠንካራ ስራ ሁለት ግቦችን ማግኘት ችለናል እነሱ ግን ሁለት ግቦችን ከምንም ማግኘት ችለዋል። ምናልባት በጨዋታው ብቸኛው በተጫዋቾቼ ቅር የተሰኘሁበት ነገር ሁለተኛዋ ግብ ላይ ስትቆጠር በግራ በኩል የነበሩ አራት ተጫዋቾቻችን ጥፋት እንዲፈፅሙ እየነገርኳቸው ያንን ማድረግ ባለመቻላችን ግብ አስተናግደናል። በዚህም በውጤቱ በጣም አዝነናል።”

በአምስቱ የሊግ ጨዋታዎች ስለ ነበራቸው እንቅስቃሴ…

“ምክንያቶችን መደርደር የምወድ ሰው አይደለሁም ፤ ከቀረቡልኝ የተለያዩ የአሰልጥነን ጥያቄዎች ኢትዮጵያ ቡናን የመረጥኩት ስብስቡ ክህሎት ባላቸው ወጣቶች የተገነባ ስለሆነ እና እነዚህ ታዳጊዎች ከፍተኛ የሆነ የማደግ አቅም እንዳላቸው ስላመንኩ ነው።ደጋግሜ እንደምለው አሁን ላይ እየተጠቀምንባቸው የምንገኛቸው ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም በጋራ ተጫውተው የሚያውቁ አይደሉም። አብዛኞቹ አምና የአሰልጣኙ እቅድ አልነበሩም ፣ ስለዚህ እኛ ገና ቡድን የመገንባቱን ሂደት ጀምረነዋል ያስመዘገብነው ውጤትም ከገጠምናቸው ተጋጣሚዎች አንፃር ጥሩ የሚባል ነው። ሊጉ ዳግም ሲመለስ አዳማ ፣ ጊዮርጊስ እና መድንን ስንገጥም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል ሌሎቹ ጨዋታዎችን ግን ማሸነፍ እንደምንችል ይሰማኛል ፣ በዚህም ዙሩ ሲጠናቀቅ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ደረጃዎች ውስጥ ማጠናቀቅን እናስባለን።”

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው…

“በሁለታችንም በኩል እጅግ ማራኪ የሆነ ፈጣን ለተመልካች ሊያዝናና የሚችል ግሩም እግር ኳስ ነበር እና በጣም ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።”

ከቆመ ኳስ ሁለቱም ጎሎች ከመቆጠራቸው አንፃር በእንቅስቃሴ ጎሎችን አለማግኘታቸው …

“በእንቅስቃሴ እኛም እነርሱም አንዳንድ ጥሩ አጋጣሚዎች ፈጥረን ነበር። የአጠቃቀም ችግር እኛም ጋር እነርሱም ጋር ነበርን እና አልተጠቀምንም። ዞሮ ዞሮ ይሄንንም ከቆመ ኳስ መጠቀም ከጎል ጋር ያለህን ነገር ለማስታረቅ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።”

ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ መጋራታቸውን እና ስለ መከላከል ድክመት…

“ድክመት አለ በራሳችን ስህተት ነው በእኛ ተከላካይ ስህተት ፣ በተለይ ሁለተኛው ጎል የተቆጠረበት መንገድ የተከላካያችን ዝንጉነት እና ጥንቃቄ ማነስ ነው።”

ስለ አምስቱ ሳምንታት ጨዋታዎች እና ስለ ቀጣዩ የዕረፍት ጊዜ…

“እንግዲ አምስቱ ሳምንታት ላይ ተጫዋቾቻችን በእንቅስቃሴ ደረጃ አምስቱም ጨዋታ ላይ ወጥ የሆነ ፈጣን እንቅስቃሴ ጥሩ የሆነ ማራኪ እግር ኳስን ጭምር ነው የሚያሳዩት እና የአጨራረስ ድክመት አለብን እርሱ ላይ በርትተን ሰርተን ፣ ለቀጣይ ለሚኖረን ጨዋታዎች ውጤታማ ስራ እንሰራለን። በተረፈ ደግሞ ልጆቻችን እጅግ በጣም ሁሉም ወጣቶች ናቸው ፣ ከልምድ ማነስ የተነሳ በድንጋጤ የሚያባክኗቸው ነገሮች ናቸው ፣ ያንን ጨዋታውን እየለመዱ ሲመጡ ቀይረን ያስገባናቸው ተጫዋቾች ጨዋታውን እንዴት እንደለወጡት ቴንፖውን እንዴት እንዳፈጠኑት አይተሀል እና ከዛም በተሻለ ሰርተን እናስተካክላለን ብዬ አስባለ።”