ከፍተኛ ሊግ | ደብረብርሃን ከተማ በዝውውሮች ራሱን አጠናክሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ የሚወዳደረው ደብረብርሃን ከተማ አስራ ሦስት ተጫዋቾችን በማስፈረም ለውድድር ዝግጁ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ተሳታፊ የሆነው ደብረብርሃን ከተማ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስር የተደለደለ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ሠለሞን አየለ እየመራ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት ወደ አስራ ሦስት የሚጠጉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን በክለቡ የነበሩ ተጨማሪ አስራ ሁለት ተጫዋቾች ውላቸው ስለመታደሱ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል።

ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾችን ስንመለከት በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ደደቢት ፣ አርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ የተጫወተው አማካዩ ታደለ መንገሻ ፣ በደቡብ ፖሊስ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ድሬዳዋ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጫወተው አጥቂው ሔኖክ አየለ ፣ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በወላይታ ድቻ ቆይታ የነበረው አማካዩ በኃይሉ ተሻገር ፣ በኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጫወተው የመስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገብረትንሣኤ ፣ በመድን እና ባለፈው ዓመት በሻሸመኔ ከተማ የነበረው ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ ፣ በሰበታ ፣ አዳማ እና ሻሸመኔ የምናውቀው አማካዩ አዲስዓለም ደሳለኝ ፣ በደቡብ ፖሊስ ፣ ሰበታ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአማካይ ስፍራ የተጫወተውን ሀብታሙ ጥላሁንን ጨምሮ ተከላካዮቹ ዑስማን መሐመድ እና ድልአዲስ ገብሬ አማካዩ ፍፁም ተስፋማርያም እንዲሁም አጥቂዎቹ አብዱልመጅድ ሁሴን ፣ አብርሃም ምህረት እና አብዱልከሪም መሐመድ ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል። 

ደብረብርሃን ከተማ ነገ 08:00 ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ቦዲቲ ከተማን በመግጠም የውድድር ዓመቱን ይጀምራል።