ከፍተኛ ሊግ | የ1ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ሲጀምር ወልዲያ ፣ አዲስ ከተማ ክ/ከ ፣ ነቀምቴ ከተማ እና ደሴ ከተማ ዓመቱን በድል ጀምረዋል።

የ04:00 ጨዋታዎች

የ2016 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በ 28 ክለቦች መካከል እንደሚደረግ ተወስኖ ዛሬ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እና በሀዋሳ ሰው ሠራሽ ሜዳ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጓል። በምድብ ‘ሀ’ ዛሬ ረፋድ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራን ጨምሮ ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች በተገኙበት የውደድር ዘመኑ የመክፈቻ ጨዋታ ተደርጓል።

ጅማ አባ ጅፋርን ከወልዲያ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ወልዲያዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቧንም ቢኒያም ላንቃሞ ከተከላካይ ተጭኖ በቀማው ኳስ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላ በተሻለ ግለት ላይ የነበሩት ወልዲያ ከተማዎች 24ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በድሩ ኑርሁሴን የጅማው ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ ለማራቅ የሞከረውን ኳስ አቋርጦ ከተቆጣጠረው በኋላ ከረጅም ርቀት ከፍ አድርጎ በመምታት ያደረገው ሙከራ መሬት ላይ ነጥሮ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ቀስ በቀስ ወደ ጥሩ እንቅስቃሴ በመመለስ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጨዋታቸውን ወደ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የቀየሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም በተሻለ የራስ መተማመን የነበረውን ጠንካራውን የወልዲያ የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተጠናክረው የቀረቡት ጅማዎች በነበራቸው መነሳሳት ላይ 52ኛው ደቂቃ ላይ ያልተጠበቀ ግብ አስተናግደዋል። ቢኒያም ላንቃሞ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ በግራ እግሩ አስደናቂ ግብ አስቆጥሮ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ አስመዝግቧል። ወልዲያዎች በሁለት ግብ ልዩነት ከመሩ በኋላ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫዎት ሲመርጡ በአንጻሩ ጅማዎች ባልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጋጣሚያቸውን ሳጥን መፈተን ቀጥለው 68ኛው ደቂቃ ላይ ቀይረው ባስገቡት ኢሳይያስ ታደሰ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። 72ኛው ደቂቃ ላይ የወልዲያን ሁለት ግቦች ያስቆጠረው ቢኒያም ላንቃሞ ከተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ በቀኝ መስመር ወደ ውጪ የሚወጣን ኳስ በእጁ በማቆሙ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወገድ የቁጥር ብልጫ ያገኙት ጅማዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው መጫወት ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በወልዲያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በምድብ ‘ለ’ በተመሳሳይ ሰዓት በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ቢሾፍቱ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተገናኝተዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የከፍተኛ ሊጉ ሰብሳቢ አቶ ሙራድ አብዲ ፣ አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ረፋድ ላይ የተከናወነውን ጨዋታ በይፋ አስጀምረውታል። ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን እና በአመዛኙም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የማጥቃት ኃይል ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጎልቶ በተንፀባረቀበት ጨዋታ 62ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱው ተከላካይ ፍፁም አለማየሁ በሳጥን ውስጥ አህመድ አብዲ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ አሰፋ ከመረብ አሳርፏት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል።

የ08:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ላይ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነቀምቴ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማን ሲያገናኝ በመጀመሪያው አጋማሽ ኮልፌዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በርካታ ቅብብሎችን በማድረግ ዝግ ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ነቀምቴዎች በአንጻሩ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረታቸውም ገና በ7ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል። የኮልፌ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው በተዘናጉበት ቅፅበት ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ኳስ ያገኘው ኢብሳ በፍቃዱ  በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ነቀምቴዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ግቧንም ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ ጨርፎ ባቀበለው ኳስ የሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ የደረሰው ተመስገን ዱባ በግሩም አጨራረስ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ በመምታት ማስቆጠር ችሏል። እንዳላቸው ጥሩ የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ኮልፌዎች በአጋማሹ አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኮልፌዎች በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተሻሽለው በመቅረብ 48ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ፈታኝ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል። ቃለጌታ ምትኩ ከ ኤርሚያስ በለጠ በተሻገረለት ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ማቲያስ ሰለሞን አግዶበታል። ከነበራቸው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመጠኑ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ነቀምቴዎች ኢብሳ በፍቃዱ 54ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረለት ኳስ ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ በግንባሩ በመግጨት ባደረጋቸው ሙከራዎች የተጋጣሚን የግብ ሳጥን መፈተን ችለው ነበር። ወጥ የሆነ አቋም ለማሳየት ተቸግረው ከነበራቸው የጨዋታ ግለት እየበረዱ የመጡት ኮልፌዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ውጤታማ አልነበሩም። 81ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው እጅግ ተቃርበው ነበር። ተከላካዮቹ እንደ መጀመሪያው ጎል ከጨዋታ ውጪ ነው በተዘናጉበት ቅፅበት ኳስ ያገኘው ቦና ቦካ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በነቀምቴ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ላይ የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ከሰዓት ቀጥሎ ደሴ ከተማ እና የመዲናይቱ ተወካይ የካ ክፍለ ከተማ ተስተናግደውበታል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በተለይ 25 ደቂቃዎችን ያህል ጥሩ ለመንቀሳቀስ የጣሩት ደሴ ከተማ የማሸነፊያ ጎላቸውን ያገኙት ገና 4ኛው ደቂቃ ነበር። አማካዩ እድሪስ ሰዒድ ወደ ሳጥን እያመራ ለነበረው ሳምሶን ተሾመ ሰንጣቂ ኳስን ሲያቀብለው ከሳምሶን ጋር ታግሎ ኳሷን ለማውጣት የጣረው የየካው ተከላካይ ወርቁ አዲስ በራሱ ጎል ላይ ኳሷን አሳርፏት ደሴዎች መሪ መሆን ችለዋል። ወደ ጨዋታ ለመመለስ የካዎች በይበልጥ ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ ገብተው ከሚታይባቸው የመረጋጋት ዕክል አኳያ ያገኟቸውን ግልፅ የማግባት ዕድሎች ወደ ጎልነት ለመለወጥ አልታደሉም።

በመጀመሪያው አርባ አምስት 35ኛው ደቂቃ ብስራት ታምሩ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግቡ አግዳሚ ብረት የመለሰበት እና ከዕረፍት መልስ 66ኛው ደቂቃ ዘላለም በረከት ከግቡ ትይዩ ሳጥን ጠርዝ ወደ ጎል የላካትን ኳስ እሸቱ ተሾመ በሚገርም ብቃት ያወጣበት የቡድኑ ጠጣሮቹ ሙከራዎቻቸው ነበሩ። የጨዋታውን የማጥቃት ፍጥነት በመልሶ ማጥቃት በማድረግ የመጨረሻውን አስራ አምስት ደቂቃ ለኋላ መስመራቸው ሽፋን ሲሰጡ ያስተዋልናቸው ደሴ ከተማዎች በመጨረሻም ተሳክቶላቸው 1ለ0 አሸንፈው ወጥተዋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ 10፡00 ሲል የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር በ ንብ እና ቤንች ማጂ ቡና መካከል ሲደረግ ንቦች ጨዋታው በተጀመረ በ 30 ሴኮንዶች ውስጥ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ኪዳኔ አሰፋ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ከግቡ አጠገብ ያገኘው ናትናኤል ሰለሞን መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። በሁለቱም በኩል ሳቢ እንቅስቃሴ እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ቤንች ማጂዎች 17ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቡንም ንቦች ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው በተዘናጉበት ቅፅበት ኳስ ያገኘው ወንድማገኝ ኬራ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተሻለ መነሳሳት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ቤንች ማጂዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ በጃፈር ሙደሲር ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ከግራ መስመር የተሻማው ኳስ በግብ ጠባቂ ሲመለስ ያገኘው ተስፋዬ በቀለ ድንቅ በሆነ አጨራረስ ከተከላካዮች ከፍ አድርጎ በመምታት አስቆጥሮታል። በጥሩ የኳስ ቅብብል ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ሲታትሩ የነበሩት ንቦቹ ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ኪዳኔ አሰፋ ከሳጥን አጠገብ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የመታው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል።

ከዕረፍት መልስ አጋማሹ በተጀመረ በ 7 ደቂቃዎች ውስጥ ቤንች ማጂዎች በዳግም ሰለሞን ከቅጣት ምት እና በእንዳለማው ድክሬ  ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራዎችን አድርገው በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣባቸው በቀሪ ደቂቃዎች ንቦች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር በጨዋታው ብልጫ ወስደዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይም ናትናኤል ሰለሞን ከ መሃል ተከላካዩ ዮሐንስ ተስፋዬ የቀማውን ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት ሲገባ ዮሐንስ ከኋላ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ኪዳኔ አሰፋ አስቆጥሮት ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎት ጨዋታውን አቻ ማድረግ ችሏል። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ 80ኛው ደቂቃ ላይ ንቦች ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ዮርዳኖስ ጸጋዬ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ምስክር መለሰ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በእግሩ መልሶበታል። ይህም የመጨረሻው የተሻለ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።

በምድብ ‘ለ’ የዕለቱ የማሳረጊያ የሆነው የጋሞ ጨንቻ እና ካፋ ቡና ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል። ከዕረፍት በፊት ደካማ እንቅስቃሴ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተን ይህ ጨዋታ ከዕረፍት መልስ በብዙ መልኩ ተሻሽሎ ያስተዋልን ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ከጎል ጋር መገያኘት ባለ መቻላቸው 0-0 ተጠናቋል።