ሀድያ ሆሳዕና ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሾሟል

ሀድያ ሆሳዕና በኢትዮጵያ ዋንጫ እና በፕሪምየር ሊጉ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ይመራል።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የጀመረው እና የሊጉን አምስት ሳምንታት የዘለቀው ሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኙ በቤተሰብ ችግር ምክንያት በገዛ ፍቃዳቸው ለክለቡ የመልቀቂያ ደብዳቤን በማስገባት መለያየታቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ክለቡ አዲስ ዋና አሰልጣኝ እስኪሾም ድረስ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምትክ አሰልጣም ግርማ ታደሠን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ መወሰኑን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።

አሰልጣኝ ግርማ ከዚህ ቀድም ሀድያ ሆሳዕናን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ ማሳደጋቸው የሚታወስ ሲሆን በመቀጠል በደበብ ፖሊስ ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ስልጤ ወራቤን በዋና አሰልጣኝነት አገልግለዋል። አሰልጣኙ ሀድያ ሆሳዕናን ከ2015 ጀምሮ በረዳት አሰልጣኝነት ሲያገለግሉም ቆይተዋል።