ከፍተኛ ሊግ | የ3ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ዛሬ አምስት ጨዋታዎች በተስተናገዱበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፉ ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል።

ሦስተኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ 03:00 ላይ በብቸኝነት ያስተናገደው በምድብ ‘ለ’ ሀዋሳ ላይ የተከናወነውን የደሴ ከተማ እና ቦዲቲ ከተማን ጨዋታ ሲሆን ቡድኖቹ ያለግብ ተለያይተዋል።

ከሰዓት 08:00 ላይ በምድብ ‘ሀ’ የሁለተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናን እና አዲስ አበባ ከተማን አገናኝቷል።  በአዲስ አበባ በኩል ኳስን በማንሸራሸር እና የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ሲንቀሳቀሱ በአንፃሩ ይርጋጨፌ ቡናዎች ስህተትን ተጠቅሞ ኳስን በመንጠቅ በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ በመድረስ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ በግብ ሙከራ ያልታጀበ ጨዋታ ተመልክተናል። ሆኖም የአጋማሹ ጥሩ የሚባል ሙከራ የጨዋታው መጀመሪያ አከባቢ አዲስ አበባ ከተማ ያገኙትን የግብ ዕድል የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ይታወሳል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ራሳቸውን ለማጠናከር የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሙከራ አርገዋል። ሆኖም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አመርቂ ያልሆነ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳንመለከት ጨዋታው መጠናቀቅ ችሏል።

በተመሳሳይ ሰዓት ሀዋሳ ላይ በተከናወነ የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ደብረብርሃን ከተማን 2-0 መርታት ችሏል። ለአዞዎቹ 15ኛ ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተገኝ እንዲሁም ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ በፍቅር ጌታቸው ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

10:00 ሲል የምድብ ‘ሀ’ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል። በወጣት ተጫዋቾች የሚመራው ጅማ አባ ጅፋር በፈጣን አጨዋወት ለመጫወት ጥረት አርጓል። ሆኖም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተመጣጣኝ አጨዋወት በፍጥነት ወደ ግብ በመድረስ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በ13ኛው ደቂቃ በተከላካይ ስህተት የተገኘውን የግብ ዕድል የኢትዮ ኤሌክትሪክ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው መሳይ ሰለሞን ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አጓጊ እና ተመጣጣኝ አጨዋወት አስመልክተውን ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጅማ አባ ጅፋር ተጭኖ ለመጫወት የሞከረበት እና ጠንካራ ጎኑን ያሳየበት አጋማሽ ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ኋላ በማፈግፈግ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክር ተስተውሏል። በዚህም አጨዋወት ጅማ አባ ጅፋር ተከታታይ የግብ ሙከራ በማድረግ የኢትዮ ኤሌክትሪኩን ግብ ጠባቂ በሽር ደሊልን ሲፈትኑት ተስተውሏል። ሆኖም ያገኙትን የግብ ዕድል ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ጨዋታው በኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ የዕለቱ ማገባደጃ የነበረው የቢሾፍቱ ከተማ እና ኦሜድላ ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾች ያስቆጠሯቸው አራት ግቦች ተስተናግደውበታል። ቢሾፍቱዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ በሰይፈ ዛኪር ጎል ቀዳሚ ሲሆኑ ኦሜድላዎች አብዱላዚዝ ዑመር ከዕረፍት በፊት እና በኋላ ባስቆጠራቸው ግቦች ጨዋታውን መምራት ችለዋል። ሆኖም የቢሾፍቱው ሰይፈ 74ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ አክሎ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።