ሪፖርት | ስታሊየኖች ዋልያዎቹን በሦስት ግብ ልዩነት ረተዋል

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቡርኪናፋሶ አቻው 3-0 ተረቷል።

የኢትዮጵያ እና የቡርኪናፋሶ ጨዋታ ቀን 10 ሰዓት ላይ ሲደረግ ዋልያዎቹ ከሴራሊዮን ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ አቤል ያለውን በማሳረፍ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ቡርኪናፋሶዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በሁለቱም በኩል ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አልተደረጉም ነበር። ሆኖም ግን በቀጥተኛ ኳስ መጫወትን የመረጡት ዋልያዎች የአጋማሹ መገባደጃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድል ፈጥረው ከነዓን ማርክነህ በዘገየ ውሳኔ አባክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ስታሊየኖች ሙሉ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በዚህም 51ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ያሬድ ባዬህ በጥሩ ቅልጥፍና አቋርጦባቸዋል። ሆኖም በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ቡርኪናፋሶዎች 69ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ተቀይሮ የገባው በርትራንድ ትራኦሬ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት መሬት ለመሬት ለኢብራሂም ብላቲ ቱሬ ሲያቀብል ኳሱን ያገኘው ቱሬም መሬት ለመሬት በመምታት በግቡ የቀኝ ክፍል በኩል ግብ አድርጎታል። ስታሊየኖች በዘጠኝ ደቂቃዎች ልዩነትም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ሚሊዮን ሰለሞን ሴድሪክ ባዶሎ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ብርትራንድ ትራኦሬ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ እንደቆመ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በሁለት ግብ ልዩነት ከተመሩ በኋላ ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም በ90ኛው ደቂቃ ልፋታቸው ላይ ውሃ የሚቸልስ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ዳንጎ ኦታራ የኢትዮጵያው ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ ከሳጥኑ ውጪ በእግሩ ለመጫወት ሲሞክር በመቀማት በቀላሉ ግብ አድርጎታል። ጨዋታውም በቡርኪናፋሶ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።