ስታሊየኖቹ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት አጥተዋል

በነገው ዕለት ኢትዮጵያን የምትገጥመው ቡርኪናፋሶ ወሳኝ ተጫዋቾቿን አጥታለች።

በመጀመርያው የምድብ ጨዋታ ከጊኒ ጋር ነጥብ ተጋርተው የማጣርያ ውድድሩን የመጀመሩት በሁበርት ቬሉድ የሚመሩት ቡርኪናፋሶዎች ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት አጥተዋል። ከጊኒ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው በሉተን ታውን የሚጫወተው ኢሳ ካቦሬ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ ከነጉዳቱ ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው የባየርን ሊቨርኩሰኑ የመሀል ተከላካይ ኤድመንድ ታፕሶባ ደግሞ በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። ቡድኑ ከዚህ ቀደምም በዩክሬኑ ሻካታር ዶኔስክ የሚጫወተው አጥቂው ላሲና ትራኦሬና የቱሉዙ ማማዱ አሌክስ ባንግሬ በጉዳት ማጣቱ ይታወሳል።

በኬፕቨርድ የሦስት ለአንድ ሽንፈት ከገጠማቸው ጀምሮ መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች ስያስተናግዱ የቆዩት አሰልጣኝ ሁበርት ቬሉድ ምንም እንኳ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ቢችሉም የተጠቀሰው ጨዋታ ጨምሮ ካደረጓቸው የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ድል ማስመዝገባቸው ከብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ እንዲበረታባቸው አድርጓል። ኢትዮጵያና ቡርኪናፋሶ በታሪካቸው ሁለት ግዜ ሲገናኙ በመጀመርያው ቡርኪናፋሶ ስታሸንፍ በሁለተኛው ግንኙነት አቻ ተለያይተዋል።