​ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ተቃኝቷል።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማዎች ቀስ በቀስ ከሊጉ መሪዎች እየራቁ በመምጣት ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ባይችሉም በአሸናፊነት የጀመሩትን የመጀመሪያው ዙር ውድድር በድል ለማገባደድ ነገ ታትረው እንደሚጫወቱ ይታሰባል። እንደ ፋሲል ከተማ የውድድር ዓመቱን በድል የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎችም በመቀመጫ ከተማቸው ካደረጓቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ካስመዘገቡት አሉታዊ ውጤት ለማገገም እና ከሚገኙበት የወራጅ ቀጠና አፋፍ ለመላቀቅ ብርቱ ትግል እንደሚያደርጉ ይታመናል።

በወጥነት ሊጉን መከወን የተሳነው ፋሲል ከነማ ከዓምናው ወረድ ያለ ብቃቱ ላይ ይገኛል። እንደ ማሳያ ዓምና በመጀመሪያዎቹ 14 የሊጉ ጨዋታዎች 32 ነጥቦችን ሰብስቦ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር በ9 ነጥቦች ቀንሶ 23 ነጥቦችን ብቻ አግኝቷል። ከሻምፒዮንነት ማግስት ባለው የውድድር ዘመን ቡድኖች ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነገር መሆኑ የማይዘነጋ ቢሆንም በደረጃ ሰንጠረዡ ያለው የነጥብ መጠጋጋት ግን በአንድ እና ሁለት ጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤት ሊፈናጠር (ከበላዩ የሚገኙ ብድኖች ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም) ይችላል። የሆነው ሆኖ ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ከቡና ጋር ሲጫወት ሦስት ነጥብ ካስረከበበት የሀዋሳ ጨዋታ በተሻለ ጥሩ የሜዳ ላይ ብቃት ሲያስመለክት ነበር። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ኳሱን ተቆጣጥሮ በሁለቱ መስመሮች ለማጥቃት ሲሞክር ነበር። በዋናነት ደግሞ ቀጥተኛ ጎሎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የቡድኑ ቀዳሚው ተጫዋች በሆነው በረከት ደስታ በኩል በተደጋጋሚ ለማጥቃት ፍላጎት አሳይቷል። ነገም በተመሳሳይ ግብ ለማግኛ የግራ መስመሩን ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ሲታሰብ የሱራፌል እና የበዛብህ መሐል ለመሐል ጥቃቶችም ለድሬዎች ፈተና እንደሚሆኑ ይታመናል።

ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ እና በሁለት ነጥቦች ብቻ ከፍ ያለው የምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች እንደ ሳሳ ነው። በመጠኑ ጥሩ እግደት እያመጣ የነበረው የኋላ መስመርም ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ እጅግ ሲፍረከረክ ታይቷል። እርግጥ ቡድኑ ጨዋታውን ለማሸነፍ ከነበረው ፍላጎት እጅግ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ተጠግቶ መጫወትን መምረጡ ተከላካዮቹ ወደ መሐል ሜዳው እንዲገፉ ያደረጋቸው ሲሆን ከእነርሱ ኋላ ያለው ሰፊ ቦታ ደግሞ ለአዳማ አጥቂዎች ዋነኛ የማጥቂያ መነሻ ሀሳብ ሆኖ ነበር። በመርህ ደረጃ ድሬ የወሰደው እርምጃ ጥሩ ሆኖ ሳለ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርገው ሽግግር ጤናማ አለመሆኑ ግን እንዲቸገር አድርጎታል። በነገው ጨዋታ እንደ አዳማው ፍልሚያ አቀራረቡ ድፍረት የተሞላበት እንደማይሆን ሲታሰብ ቀጥተኝነትን ግን ሊያዘወትር እንደሚችል ይገመታል። በዚህ ሂደት የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ለፋሲል በመስጠት የመልሶ ማጥቃቶችን እና ቁመታሙን አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ዒላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ለግብ ምንጭነት ሊጠቀም ይችላል ተብሎ ይታሰባል። የፋሲል ተከላካዮች ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ብቃት መውረድ እና ፍጥነት መቀነስ ደግሞ ለቡድኑ ዋጋ ሊሰጥ ይችላል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጣምራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ የሆነው ፋሲል እስካሁን ካከናወናቸው አስራ አራት ጨዋታዎች ሦስቱ ላይ ብቻ ነው ተጋጣሚ ላይ ግብ ሳያስቆጥር የወጣው። ያስመዘገባቸውን 21 ጎሎች ደግሞ ዘጠኝ ተጫዋቾች ያስቆጠሩት ሲሆን በቦታ ለግብ የቀረበ አጥቂ እስካሁን የቡድኑ አስተማማኝ የግብ ምንጭ አለመሆናቸው ግን የሚያሳስበው ይመስላል። ድሬዳዋም በተመሳሳይ በወጥነት ሳምንት በሳምንት ኳስ እና መረብን የሚያገናኝለት የጎል አዳኝ የለውም። እርግጥ ማማዱ ሲዲቤ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቢሆንም ተጫዋቹ የመጨረሻ ጎሉን ካገባ አስር ጨዋታዎች አልፈዋል። ይህ ወጥ የመሐል አጥቂ ችግር ነገ ቡድኖቹን ምን ያህል ሊጎዳ ይችላል የሚለው የሚጠበቅ ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያሉት ፈጣኖቹ የመስመር ተጫዋቾች ግን ጉልህ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ይታመናል።
ፋሲል ከነማ ሰዒድ ሀሰን እና ኪሩቤል ኃይሉን በጉዳት ምክንያት ነገ የሚያጣ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ የግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁንን ብቻ በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ያደርጋል። በዐፄዎቹ በኩል ከቀናት በፊት ወደ ስብስቡ የተቀላቀለው ሙጂብ ቃሲም ምናልባት በጨዋታው የመሳተፍ ዕድል ሊሰጠው እንደሚችል ተመላክቷል።

ፋሲል ከነማ ወደመሪዎቹ ለመጠጋር ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያደርጉትን ጨዋታ ተከተል ተሾመ በመሐል አልቢትርነት ሸዋንግዛው ተባበል እና ወጋየሁ አየለ ደግሞ ረዳት ተፈሪ አለባቸው በበኩላቸው አራተኛ ዳኛ ሆነው ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሊጉ ስምንት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ ደግሞ ሁለቱን አሸንፏል። ፋሲል 7 ፣ ድሬዳዋ 5 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ 


ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሃን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – በዛብህ መለዮ – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ


ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ደረጄ ዓለሙ

እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ዳንኤል ደምሴ – ዳንኤል ኃይሉ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ

ማማዱ ሲዲቤ