ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን ጨዋታ ይመራል

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ጋቦን ለምታዘጋጀው የ2017 አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚዳኙ ዳኞችን ሾሟል፡፡ ኢትዮጵያዊው የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በምድብ 13 ካሜሮን ከደቡብ አፍሪካ ያውንዴ ላይ መጋቢት 17 የሚያደርጉትን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት እንዲመራ የተመረጠ ሲሆን ረዳቶቹ ክንዴ ሙሴ እና ተመስገን ሳሙኤል ሲሆኑ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ለ1 አመት የታገደው ለሚ ንጉሴ 4ኛ ዳኛ ሆኗል፡፡

ባምላክ ሩዋንዳ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ (ቻን) ላይ በመሃል እና አራተኛ ዳኛ ሆኖ ጨዋታዎችን የመራ ሲሆን የአህጉራዊ እና የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ እየዳኘ የሚገኘው የፊፋ ኢንተርናሽናል አርቢትር የሆነው ባምላክ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡

የብሄራዊ ብድን ጨዋታዎችን ስለመምራቱ

“የተለየ ሚስጢር የለውም፤ የደረጃ ጉዳይ ነው፡፡ ሌሎች የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን፣ ከ20 ዓመት በታች እና የአህጉር የክለብ ጨዋታዎችን የሚያጫውቱ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች አሉ፡፡ ሃገራችን ቀደምት በጣም ታዋቂ ዳኞች የነበሩባት ናት ከዚህም በላይ ያጫወቱ ዳኞች የነበሩ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሃገራችን ተቀጥታ ነበር፡፡ “አሁን ባለው ደረጃ በካፍ ኤሊት ዳኞች የሚባል ፓናል አለ፡፡ ካፍ ዳኞችን በተለያየ ደረጃ የሚከፍልበት መንገድ አለ፡፡ እኔ ኤሊት ኤ የሚባለው ደረጃ ላይ ነው የምገኘው፡፡ በየደረጃው የጨዋታ ምድብ በሚሰጥበት ጊዜ ምደባው ስለደረሰኝ ጨዋታዎችን ለማጫወት ችያለሁ፡፡ ”

የባምላክ በአህጉራዊ ውድድሮች መዳኘት ለሌሎች የኢትዮጵያ ዳኞች ስለሚፈጥረው እድል

“አሁን ባለው ደረጃ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ የወጣት እና በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና የሚያጫወቱ፤ በደረጃ ከኔ በታች ባሉ እንዲሁም ከኔ ጋር ያሉ ዳኞች አሉ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ የሚያጫውቱ ወንዶችም እና ሴቶችም ደግሞ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ድረስ የሄዱ አሉ፡፡ ከነሱ ጋር በጋራ ነው የምንሰራው፡፡ እግርኳስ ዳኝነት የቡድን ስራ ነው፡፡ አሁን እኔ የተለየ ነገር ስለሰራው ሳይሆን የጋራ ድምር ውጤት ነው፡፡ ብሄራዊ ፌድሬሽኑም ለዳኝነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ስለሚንቀሳቀስ ለዳኞች የተሻሉ የውጪ እድሎች እየመጡ ያሉት፡፡ ”

IMG_4381

የኢትዮጵያ ዳኞች በኢንተርናሽናል መድረክ ስለሚኖራቸው የወደፊት ሁኔታ

“ሃገራችንን ያስጠሩ ብዙ ዳኞች አሉ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ እኔ እስከማውቀው ድረስ እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ እና ግማሽ ፍፃሜ ያጫወቱ ስመጥር ዳኞች ያሉበት ሃገር ነው፡፡ ይህንን ስም መመለስ ቀላል አይደለም፡፡ ለመመለስ ረጅም ግዜም ወስዷል፡፡ ግን አሁን ባለው ሁኔታ እና ሂደት ስማችን ለተከታታይ 11 እና 12 ዓመት አልነበረም፡፡ አሁን ግን የአፍሪካ ዋንጫ እና በሴቶች የዓለም ዋንጫ የሚያጫውቱ ሴት ዳኞች አሉ፤ ይህ በፊት ያልነበረ ነው፡፡ በባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ (በ2015 የኢኳቶሪያል ጊኒ የአፍሪካ ዋንጫ) በዳኝነት ተሳትፈናል በቻንም ጨምሮ ተሳትፈናል፡፡ ቀጣዩ ጊዜ ብሩህ ነው ብዬ አስባለው፡፡ ያው መስራት እና ኃላ የቀረንበትን ግዜ ቶሎ ለመሸፈን መጣር ይጠይቃል፡፡ ”

ስለወደፊት እቅዱ

“መመኘት በሰፖርቱ ውስጥ ያለ ነው፡፡ እግርኳስ ተጫዋቾች ያላቸው ህልምም በአንድ ታላቅ ክለብ ወይም በታላቅ ሊግ መጫወት ነው፡፡ በዳኝነትም እንደዛው ነው፡፡ በሙያው በጣም ትላልቅ በሆኑ ውድድሮች መዳኘት ትላልቅ በሆኑ ማጣሪያዎች ማጫወት ከዚያም በላይ የአለም ውድድሮች ላይ ማጫወት እፈልጋለው፡፡ ያንን ለመተግብር ግን በጣም ከባድ ስራ እና ፉክክር ይጠይቃል፡፡ ”

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *