የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት የዛሬ ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም መደረጋቸውን ሲቀጥሉ ሀዋሳ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን አሳክቷል። አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማም ድል አስመዝግበዋል።

ጎንደር ላይ እየተካሄደ በሚገኘው የምድብ ሀ 8፡00 ላይ ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠመው የዓምናው ቻምፒዮን አዳማ ከተማ 2-0 ማሸነፍ ችሏል።

ጥሩ የውድድር ጅማሮ ባያደርጉም በሂደት እየተሻሻሉ የመጡት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ተደጋጋሚ ኳሶችን ቢያመክኑም አሸንፈው መውጣት የሚችሉባቸውን ግቦችን ከማግኘት አልገደባቸውም ። 52ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ታረቀኝ ከርቀት ግሩም የቅጣት ምት አስቆጥሮ አዳማን ቀደሚ ማድረግ ሲችል 62ኛው ደቂቃ ላይ ተከተል በዙ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ በማስቆጠር አዳማ ከተማዎች 2 – 0 አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

10:00 የተደረገው የባህር ዳር ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። አሰልቺ እና ግጭት የበዛበት የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የረባ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ በ አርባምንጭ ከተማ በኩል 55ኛው ደቂቃ ለይ በቀኝ ሳጥን ጠርዝ የተገኘውን ቅጣት ምት አስቻለው ስሜ ወደ ግብ ሞክሮግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚጠቀስ ነበር ። በባህርዳር በኩል 88ኛው ደቂቃ ላይ ኪዳነማርያም ተስፋዬ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደግብ በቀጥታ የሞከረው የሚጠቀስ ነበር።

አሰላ ላይ እየተደረገ በሚገኘው የምድብ ለ ውድድር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን አስቀድሞ የተያዘላቸው ሰዓት 8፡00 እና 10፡00 ቢሆንም በስታዲየሙ የአትሌቲክስ ውድድር የሚካሄድ በመሆኑ ረፋድ ላይ እንዲካሄዱ ተደርጓል።

2፡30 ላይ ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን ገጥሞ 2-1 አሸንፏል። ስጦታው ዓለማየሁ በ70ኛው እንዲሁም ናትናኤል አርጋኖ በ81ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳን የድል ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሙከረም ምዕራብ በ33ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ጎል አስቆጥሯል። ይህ ድል ለሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ሦስተኛ ድል መሆንም ችሏል።

4፡30 ላይ ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ፋሲል ከነማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ጎል የዘለቀው ጨዋታ በአፄዎቹ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ያደረገች ወሳኝ ጎል በጭማሪው ሦስተና ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሳምሶን ዘርዓይ ነው።