‹‹ተጫዋቾቻችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ለማሳየት ተዘጋጅተዋል›› የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው

በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የአልጄርያ አቻውን ነገ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያደርጋል፡፡ ብሄራዊ ቡኑ ባረፈበት አፋረንሲስ ሆቴል የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር በነገው ጨዋታ ዙርያ ቡድኑ ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ ቆይታ አድርጋለች፡፡

በአልጀርሱ ጨዋታ የቡድናችን ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድን ነበር የተጋጣያችንስ ?

በአልጄርየው ጨዋታ የነበሩን ጠንካራ ጎኖች በርካታ ነበሩ፡፡ በጨዋታው የነበራቸው ትንካሽ ፣ ጨዋታ የመቆጣጠር እና ለተጫዋቾቻን የሰጠናቸውን ተግባራት በሜዳ ላይ መከወን ላይ ጥሩ ነበርን ብዬ አስባለሁ፡፡ ምናልባት እንደ ድክመት የምቆጥረው ጎል ሳናስቆጥር መመለሳችን ላይ ነው፡፡ እንደ ግብ ይነው የሄድነው ግብ አስጥረን ለመመለስ ነበር፡፡ በጨዋታው ላይም ሙከራዎች ማድረግ ችለን ነበር፡፡ ከአልጄርያ መልስ የግብ ማስቆጠር ላይ ስንሰራ ቆይተናል፡፡

በአልጄሪያ በኩል የመጀመርያው ጠንካራ ጎናቸው ፕሮፌሽናል አስተሳሰባቸው ነው፡፡ ተጫዋቾቹ በአውሮፓ እና በጠንካራው የሊግ መዋቅራቸው ውስጥ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ የቆሙ ኳሶች እና አንድ ለአንድ አጋጣሚዎች ላይ ጠንካራ ናቸው፡፡ እንደ ድክመት የተመለከትንባቸው ደግሞ ኳስ ቁጥጥር ላይ ደካማ መሆናቸውን ነው፡፡ ሌላው ለእኛ ዝቅተኛ ግምት መስጠታቸውን በጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸው ላይ ሰምተናል፡፡ ከጨዋታው በኋላ ግን የሰጡን ግምት የተሳሳተ እንደሆነ አይተዋል፡፡

የመልሱን ጨዋታ አሸንፈን ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ያለን ዝግጁነት ምን ያህል ነው ?

ይህን ብሄራዊ ቡድን በሶስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ከ2006 የደቡብ አፍሪካ ውድድር ጀምሮ በብሄራዊ ቡድኑ በመጫውት ላይ የሚገኙ ፣ ከዛ በኋላ የመጡ ተጫዋቾች እና ከወጣት ብሄራዊ ቡድኖች የተመረጡ ተጫዋቾች የተካተቱበት ስብስብ ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ከተለያየ ትውልድ የተሰባሰቡ ቢሆንም ፍላጎታቸው እና ተነሳሽነታቸው ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደሚችሉ እና ማሸነፍ እንደሚችሉ ለማሳየት ተዘጋጅተዋል፡፡

ከአልጄርያ መልስ ቡድኑ ሙሉ ትኩረቱን በማጥቃት ላይ አድርጎ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ የተከላካይ መስመሩ አልተዘነጋም ?

ከአልጄርያ ተሸንፈን መምጣታችን መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ እዚህ ግቦች ማስቆጠር ይጠበቅብናል፡፡ የተከላካይ መስመራችን ደግሞ ጠንካራ ነው፡፡ ወደ አልጄርያ ከመሄዳችን በፊት በተከላካይ ክፍችን ላይ ጠንክራ ስራዎች ሰርተናል፡፡ በዝግጅታችን ላይ ስንመለከታቸውም በጥሩ መንገድ እየተጓዙልን ነው፡፡ ግብ ካስተናገድን አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ ስለምንገባ በጥንቃቄ መጫወቱን አንዘነጋውም፡፡

በስነ ልቦናው ረገድ ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል?

በስነ ልቦናው ረገድ የባለሙያ ምክር እዲያገኙ አድርገናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም በራሳቸው ከፍተና በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ጠዋት (ትላንት) ላይ ተነጋግረናል፡፡ ጨዋታውን ለማሸነፍ ያለፉ የወንዶችም ሆነ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ስኬቶች እንደ ማነሳሻ ለመጠቀም ሞክረናል፡፡

በኢትዮጵያ ቡድኖች በተደጋጋሚ የተመለከትነው ሙሉ ጨዋታን በትኩረት ያለመጫወት ችግር ለመቅረፍ ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል?

እኔ በብሄራዊ ቡድን 4 አመት ከ6 ወር ሰርቻለሁ፡፡ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ብዙ የቆዩ ተጫዋቾችም አሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ልምድ ያካፍላሉ ብለን እናስባለን፡፡ ከ17 አመት በታች ቡድኑ ከውድድሩ የወጣበት መንገድን በማንሳት ከተጫዋቾቹ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ብዙ ጊዜ ከሜዳችን ውጭ ጥሩ ውጤት አስመዝግበን ብንመጣም በሜዳችን መጠቀም የሚገባንን እድቫንቴጅ ሳንጠቀም ቆይተናል፡፡ በብዙ ጥረት ግብ ብናስቆጥርም በጥቃቅን ስህተት እና የትኩረት ችግር ግቦች በቀላሉ ግቦች እናስተናግዳለን፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይከሰት ሙሉውን 90 ደቂቃ በትኩረት እንጫወታለን፡፡

PicsArt_1458890733153

በመጀመርያው ጨዋታ እንደተመለከትነው የአልጄርያ ቡድን በኋላ መስመሩ ላይ ድክመት ይታይበታል፡፡ ይህንን ለመጠቀም ቡድናችን ምን አይነት ቅርጽ ይኖረዋል?

በጨዋታው ሶስት አጥቂዎችን ከፊት በማድረግና ለነሱ ብቻ ሀላፊነት በመስጠት ከነሱ ጎል መጠበቅ ብቻ ላይ አናተኩርም፡፡ እንደ ቡድን የምናጠቃበት ፣ የግብ እድሎች የምንፈጥርበት እና ግቦች የምናስቆጥርበት እንቅስቃሴ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡ ሌላው ግብ ጠባቂዋ ድክመት ያለባት ብትመስልም ጠንካራ ግብ ጠባቂ ናት፡፡ የቆሙ ኳሶች ላይ ያላት የቦታ አጠባበቅ እና ጥንቃቄ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ኳሶችን የመትፋት ችግር ስላለባት ያንን ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን፡፡ በተጨማሪም አልጄርያዎች የለመዱት ጠባብ ሜዳ ነው፡፡ አዲስ አበባ ስታድየም ደግሞ ሰፊ ሜዳ ያለው በመሆኑ ብዙ ስህተት እንዲፈጥሩ ያደርጋቸዋል ብለን እናስባለን፡፡

በመጀመርያው ጨዋታ ላይ (በተለይም ኤደን) ለጨዋታ ብቁ ያልሆኑ ተጫዋቾችን ስንመለከት ነበር፡፡ የአማካይ መስመር ጥምረቱም አስደሳች አልነበረም፡፡ በመልሱ ጨዋታ ለውጦች እንጠብቅ?

የኤደን የሜዳ ላይ አገልግሎት ከፍተኛ ነው፡፡ ከሜዳችን ውጪ በመጫወታችንም የመከላከል ባሀርይ ያላቸው ተጫዋቾችን ለማብዛት በሚል ነው ሁለት የተከላካይ አማካዮች የተጫወትነው፡፡ በነገው ጨዋታ ግን ማጥቃት ላይ ለሚያተኩሩ ተጫዋቾች እድል እንሰጣለን፡፡ በጨዋታው ላይ ለጨዋታ ብቁ ያለመሆን እና የታክቲክ ዲሲፕሊን ላይ ድክመቶች ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ በነገው ጨዋታ ብቁ የሆኑ ተጫዋቾች ይሰለፋሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *