የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እጣ ፈንታውን የሚወስኑ ሁለት ጨዋታዎች ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል፡፡ በዛሬው እለትም የመጀመርያውን ጨዋታ ምሽት 4፡30 ላይ ያደርጋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አልጄርያ ሊጓዝ በሚሰናዳበት ወቅት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረገው አዲሱ የቡድኑ አምበል አስራት መገርሳ ለአልጄርያ ከፍተና ግምት ቢሰጥም በጨዋታው ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን እንደተዘጋጁ ተናግሯል፡፡
‹‹ ሁሉንም ጨዋታ የምናደርገው ውጤት ለማግኘት ነው፡፡ ጠንካራ ተፈካካሪ ሆነን በመቅረብ ጥሩ ውጤት ይዘን እንደምንመለስ አስባለሁ፡፡ በሁለቱ ተከታታይ ጨዋታዎችም ነጥቦች ይዘን እንወጣለን ብዬ ነው የማስበው፡፡
‹‹ አልጄርያ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ይህንን ሁላችንም የምናምነው ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እኛም ተፎካክረን ውጤት ይዘን ለመመለስ ነው የምንሄደው፡፡ እኔ በግሌ የትኛውንም ቡድን አልፈራም፡፡ በእግርኳስ የሚፈጠሩ ነገሮችም አይታወቁም፡፡ ይህ ሀሳብ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የቡድን አባላት እንደሚሆን እምነት አለኝ፡፡ ለአልጄርያ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እግርኳስ ላይ ግምት ሳይሆን የሜዳ ላይ እቅስቃሴ ነው ወሳኙ ነገር፡፡ ስለዚህ እጅግ አግዝፈን የምንመለከትበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን ጠንካራ ቡድን በመሆኑ ጠንክረን መጫወት እንዳለብን አምናለሁ፡፡››
ስዩም ተስፋዬ በጉዳት ከቡድኑ ውጪ መሆኑን ተከትሎ ቡድን በአምበልነት እንዲመራ በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የተመረጠው አስራት መገርሳ አምበልነቱን ተጠቅሞ ቡድኑን ለማነሳሳት ጥረት እደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
‹‹ ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት ለመምራት ስመረጥ ሊኖረኝ የሚችለውን ደስታ መገመት አያዳግትም፡፡ አንድ ተጫዋች አምበልነት ሲመረጥ አሰልጣኙ አምኖበት ነው፡፡ ከልምድ አንጻር ጥሩ ልምድ አለኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ያንን ልምድ ተጠቅሜ ቡድኑን በማነሰሳት ውጤታማ እንዲሆን ጥረት አደርጋለሁ፡፡›› የሚለው አስራት በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ለኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች እድል ሊፈጥር የሚችል እንደሆነ ያምናል፡፡
‹‹ አልጄርያ ትልቅ ቡድን በመሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ተከታታይ ይኖረዋል፡፡ አልጄርያን ለመከታተል የሚመጡ መልማዮች የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን የመመልከት አጋጣሚንም ይፈጥርላቸዋል፡፡ በጨዋው ጥሩ የሚንቀሳቀስ ተጫዋች በመልማዮች እይታ ለመግባት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርለታል ብዬ አስባለሁ፡፡›› ይላል፡፡
አስራት በመጨረሻም በጨዋታው ውጤታማ ለመሆን ከግል እንቅስቃሴ ይልቅ ከአሰልጣኛቸው የሚሰጣቸውን መመርያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግሯል፡፡
‹‹ እንደተጫዋች የኛ ሀላፊነት የሚሆነው የአሰልጣኛችንን ታክቲክ መተግበር ነው፡፡ በጨዋታ ሂደት የሚፈጠሩ ለውጦችን ተከትሎ በግል ሊደረግ የሚችል እንቅስቃሴ ቢኖርም ቅድሚያ የምንሰጠው የአሰልጣኛችንን እቅድ መተግበር ላይ ነው፡፡ እኔ በግሌ ይህን ብናደርግ ብዬ የማስበው ነገር አይኖርም፡፡ ››