አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ለክለቡ ደብዳቤ አስገብተዋል

የሀድያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት “ክለቡን ለጠየኳቸው ጥያቄዎች መልስ ካላገኘሁ ኃላፊነት አልወስድም” በሚል ደብዳቤ አስገብተዋል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መሪነት በዘንድሮው የ2014 የውድድር ዘመን ጉዞውን እያደረገ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና በመጀመሪያው ዙር የአስራ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎች በ17 ነጥብ 12ተኛ ደረጃን በመያዝ ዙሩን ማገባደዱ ይታወሳል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከተጫዋቾች እና ከአሰልጣኞች ክፍያ ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ለዕግድ ሲዳረግ እየተመለከትነው የምንገኘው ክለቡ ነገ በአዳማ ሳይንስ እና ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም 12፡00 ሰዓት ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የሁለተኛውን ዙር ውድድር በይፋ ይጀምራል፡፡

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ግን በዛሬው ዕለት ለሶከር ኢትዮጵያ ለክለቡ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ በዋናነት በደብዳቤው በአቤቱታ መልክ ባሰፈሩት ፅሁፉ ስብስባቸው ለሁለተኛው ዙር እንዲጠናከር አዳዲስ ተጫዋቾችን ክለቡ እንዲያስፈርም ጥያቄ በተደጋጋሚ ማቅረባቸውን እና ተፈፃሚ አለመደረጉን በመጥቀስ በቀጣይ ክለቡ ይሄን ጉዳይ በቀናት ካልተፈታ ሀላፊነት እንደማይወስዱ አመላክተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ አግኝተን ተከታዩን ሀሳብ በምላሻቸው ነግረውናል፡፡

“አንድ የውጪ ተጫዋች ነገ ማታ ይገባል። ይህንንም ጉዳይ እየጨራረስኩ ነው፡፡ አንድ ተከላካይም ከሀገር ውስጥ ልናመጣ ነው፡፡ እሱን በቀጣይ ቀናት እናሳውቃለን አሰልጣኙ የጠየቀውን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራን እንገኛለን፡፡ በአጠቃላይ ቡድኑ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለማስተካከል በምንችለው አቅም እየጣርን ነው፡፡” ሲሉ አጠር ምላሽን ሰጥተውናል፡፡