የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 አዳማ ከተማ

በከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ታጅቦ ከተካሄደው አዝናኙ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡት አስተያየት እንደሚከለው ይነበባል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታ እንቅስቃሴያቸው

“ሙሉ ለሙሉ አግኝተናል ለማለት እቸገራለሁ። ነገርግን ልጆቻችን ያላቸውን ነገር ለማስቀጠል የነበራቸው ጥረት ጥሩ ነው። ተጋጣሚያችን ጠንካራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንቅስቃሴያችን ይቆራረጥ ነበር። ከዚህ አንፃር ሙሉ ለሙሉ ጥሩ ነን ማለት አልችልም።

ስለ ያሬድ ታደሰ ቅያሬ

“ያሬድ ከሀዘን ነበር የተመለሰው። በዚህም በጨዋታ ዝግጁነቱ ላይ እርግጠኛ አልነበርንም። የተጎዱ ልጆች ስለነበሩ ነበር በቋሚነት ያስጀመርነው ለዚህም ነበር ፤ ቅያሬውን ለማድረግ የተገደደነው።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበራቸው እንቅስቃሴ

“በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻልን ነበርን በሁለተኛው ግን እነሱ የመጀመሪያውን እንዳናስቀጥል ይዘውት የመጡት ጨዋታ ትንሽ ከብዶን ነበር።

ስለ ሮበርት እና ሰዒድ ፉክክር

“ዛሬ ሰዒድ ያሳየው ብቃት ለሮበርት ትልቅ መልዕክት ነው። ሮበርት ትልቅ ግብ ጠባቂ ነው ፤ ትልቅ ስለሆነ ብቻ አናሰልፈውም። ብቃትን መሰረት ያደረገ የተጫዋች ምርጫ እናደርጋለን። ሰዒድ በዚሁ ከቀጠለ የማይጫወትበት ምክንያት አይኖርም።”

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ስለ ውጤቱ

“ከባድ ጨዋታ ነበር ፤ ማሸነፍ ፈልገን ነበር። ዕኩል በመውጣታችን ደስተኛ አልነበርኩም። በመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ጫና ውስጥ ገብተን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ያንን ለማረም ሞክረን ነበር። ከሞላ ጎደል ጨዋታው ጥሩ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ስለመሆናቸው

“አንዳንድ ኳሶች በበረኛ ጥንካሬ ነው አንዳንዶቹ ደግሞ በችኮላ የተሳቱ ናቸው። እንደቡድን ግን ተመርተን ልዩነቱን ገልብጠን ተጋጣሚ ሳጥን ደርሰን ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠራችንን በጥሩ ጎን አየዋለሁ።

10ኛ አቻ ስለማስመዝገባቸው

“ይህን ነገር በእርግጠኝነት እዚህ እንቀይረዋለን ብዬ አስባለሁ። ይሄ እኔን ተጫዋቾቹንም ጫና ውስጥ ያስገባል። ታድያ ተከታታይ ድሎች አስመዝግበን ከዚህ ካልወጣን በስተቀር ተጫዋቾቹ በዚህ ስሜት ውስጥ እንዳሉ አውቃለሁ። ግን ሜዳ ላይ ደጋፊውን ለማስደሰት እና ውጤት ለማስመዝገብ የነበራቸው ተነሳሽነት በጣም ጥሩ ነበር።

ስለ ደጋፊዎች ድባብ

“ከረጅም ጊዜ በኋላ ይህን ነገር ማየታችን አዲስ ነገር ነው። የስታዲየም ውበት እና ህይወት የሆኑት ደጋፊዎችን በዚህ መልኩ በማየቴ ደስተኛ ነኝ።”