የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በሁለተኛው ፅሁፋችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ቀርበውበታል።

👉 የሀይደር ሸረፋ አላስፈላጊ ድርጊት

በሊጉ አብዛኞቹ የማስጠንቀቂያ ካርዶች ቡድንን በማይጠቅሙ አላስፈላጊ የተጫዋቾች ባህሪ የሚመዘዙ ስለመሆናቸው ለመታዘብ ሀይደር ሸረፋ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣበትን ሂደት ማየት በቂ ነው።

በጨዋታ ሳምንቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ በጋቶች ፓኖም አማካኝነት ባስቆጠሯት ግብ ጨዋታውን እየመሩ በነበረበት ሂደት በ75ኛው ደቂቃ ላይ ያልተጠበቀ ነገር ተፈጥሯል።

ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት እያደረጉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ75ኛው ደቂቃ ናትናኤል ዘለቀን በሀይደር ሸረፋ ተክተው ወደ ሜዳ ለማስገባት ይፈልጋሉ። በዚህ ሂደት የሚቀየረው ሀይደር ሸረፋ የአምበልነት ምልክቱን ለቡድን አጋሩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ካጠለቀለት በኋላ በዳኛው በአቅራቢያው በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ አጠገብ እንዲወጣ በተነገረው ወቅት ባሳየው ምላሽ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከተ ሲሆን በዚህ ያላበቃው ተጫዋቹ ለዳኛው ውሳኔ በስላቅ ማጨብጨቡን ተከትሎ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ በቅቷል።


ከሜዳ በቀይ ካርድ መውጣት ከስፖርቱ ፅንሰ ሀሳብ አንፃር የሚበረታታ ድርጊት ባይሆንም ቀይ ካርዶቹ ለቡድን ጥቅም ሲባል ከሚወሰኑ የተጫዋቾች ውሳኔዎች አንፃር ከተመለከትነው ምናልባት ለቡድኑ ከነበራቸው ትሩፋት አንፃር “ተገቢ ነበር” ልንል ብንችልም እንደ ሀይደር ደግሞ ለቡድኑ ፍፁም ጥቅም የሌላቸው የግላዊ ስሜት ማስታመሚያ የሆኑ ቀይ ካርዶችን ግን ማውገዝ ይገባል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ጫና ውስጥ በወደቀባቸው በእነዚያ የጨዋታ ደቂቃዎች የቡድኑን የመከላከል አቅም ለማሳደግ በአሰልጣኝ ቡድን አባላት የታመነበት ለውጥ ለማድረግ ቡድኑ በተዘጋጀበት ወቅት ባልተገባ ድርጊት የወጣው ሀይደር የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ቡድኑ በጎደሎ ተጫዋቾች እንዲጫወት አስገድዷል። በመሆኑም አሁንም ቢሆን ተጫዋቾች ከግል ስሜት ባለፈ ስለ ቡድናቸው በማሰብ መሰል ከቸልተኝነት ከሚመነጩ ድርጊቶች ሊቆጠቡ ይገባል።

👉 ተቀይሮ እንደገባ ያስቆጠረው አዲሱ አቱላ

መከላከያ ከባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ጨዋታዎች መከላከያዎች አስቀድመው ግብ ቢያስተናግዱም አዲሱ አቱላ ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ታድያ መከላከያዎች የአቻነቷን ግብ ያገኙበት መንገድ አስገራሚ ነበር። የአቻነት ግብ እያሰሱ የነበሩት መከላከያዎች በ68ኛው ደቂቃ ላይ ኢማኑኤል ላርያ በተሰራው ጥፋት የቅጣት ምት ያገኛሉ። ጨዋታው መቋረጡን ተከትሎ መከላከያዎች አጥቂያቸውን ባድራ ሴይላን አስወጥተው በምትኩ አዲሱ አቱላን ያስገቡበትን ለውጥ ያደርጋሉ።

ተቀይሮ የገባውም አዲሱ አቱላ የመጀመሪያ ተሳትፎን ለማድረግ ወደ ሳጥን ይገሰግሳል ፤ በዚህ ቅፅበት ከግራ መስመር ቢኒያም በላይ እግር የተሻማውን ኳስ በሩቁ ቋሚ አካባቢ የነበረው እስራኤል እሸቱ ወደ ውስጥ የገጫትን ኳስ አዲሱ አቱላ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ተቀይሮ ከገባ በኋላ አስራ አምስት ሰከንዶች ያነሰን ቆይታ ያደረገው አዲሱ አቱላ በመጀመሪያ የኳስ ንኪኪው ያስቆጠራት ግብ በሳምንቱ ትኩረት ከሳቡ አጋጣሚዎች አንዷ ነበረች። በአስገራሚ መልኩ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ20ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ጋር አቻ ሲለያዩ 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው በላይ አባይነህ በመጀመሪያ ንክኪው በቀጥታ ከቅጣት ምት ቡድኑን አቻ ያደረገች ግብ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

ከዚህ ባለፈም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ባህርዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታም ላይ እንዲሁ ሳላአምላክ ተገኘ ተቀይሮ እንደገባ በመጀመሪያ የኳስ ንኪኪው ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር መቻሉ ይታወሳል።

👉 ሄኖክ ኢሳይያስን ለመተካት የተቸገረው ድሬዳዋ ከተማ

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ሄኖክ ኢሳያስን አሳልፈው የሰጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በቦታው ሁነኛ ተተኪ ለማግኘት ተቸግረዋል።

በ2012 አጋማሽ የዝውውር መስኮት መቐለ 70 እንደርታን ለቆ ድሬዳዋ ከተማን ከተቀላቀለ ወዲህ በግራ የመስመር ተከላካይነት ቡድኑን ላለፉት ጊዜያት በብቃት ሲያገለግል የነበረው ሄኖክ አሁን ላይ ድሬን ለቆ መሄዱን ተከትሎ አዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ ይህን ቦታ ለመሸነፍ በርካታ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛል።

በዝውውር መስኮቱ ክለቡን የተቀላቀለው አማረ በቀለ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል ቢያገኝም አሰልጣኙን ማሳመን ሳይችል ቀርቷል። በቀጣይ በነበሩት ጨዋታዎች የመስመር አማካዮቹ አብዱለቲፍ መሀመድ እና ጋዲሳ መብራቴን ጨምሮ ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከወልቂጤ ጋር አቻ ሲለያይ በሁለተኛው አጋማሽ ወጣቱን ያሲን ጀማልንም በዚህ ስፍራ ሲጠቀም ተመልከተናል።

የቅርፅ ለውጦቹን ትተን የተደረጉት ግለሰባዊ ለውጦችን ብቻ ከተመለከትን ቡድኑ ይህን የግራ መስመር ተከላካይ /ተመላላሽ/ ስፍራ ላይ ሁነኛ ሰው ለማግኘት መቸገሩን እየተመለከተን እንገኛለን። ከዚህም ባለፈ ይህን የቡድኑ ክፍል በተደጋጋሚ የተጋጣሚ ቡድኖች የጥቃት ኢላማም ተደርጎ እንዲሁ እየተመለከትን እንገኛለን።

👉 በዛብህ መለዮ ፋሲልን መታደጉን ቀጥሏል

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማ አርባምንጭ ከተማን በመርታት በሰንጠረዡ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ያለበትን ድል ሲያስመዘግብ የበዛብህ ግብ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ነበረች።

አማካዩ በዛብህ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የተጠናቀቀውን የጨዋታ ሳምንት ሳምንት ጨምሮ ለ1295 ደቂቃዎች ያህል በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች በድምሩ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ከአጥቂው አኪኪ አፎላቢ ጋር በጣምራ የፋሲል ከነማ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን ችለዋል።

በሊጉም ሰባት ግቦችን ካስቆጠረው ፍፁም ዓለሙ ቀጥሎ ከፍተኛው ግብ አስቆጣሪ አማካይ መሆን ችሏል ፤ ታድያ የበዛብህ ስድስት ግቦች ለፋሲል ከግብ በላይ ዋጋ አላቸው።

ፋሲል ከነማ በበዛብህ መለዮ ግቦች ጅማ አባ ጅፋርን 4-0 ሲረቱ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ውጭ ቡድኑ በእሱ ግብ ቀጥታ ስምንት ነጥቦችን ማሳካት ችለዋል ይህም ተጫዋቹ ለቡድኑ ያለውን አስፈላጊነት በጎልህ የሚያሳይ ነው።

ከጥልቀት በመነሳት ዘግይቶ ወደ ሳጥን በመፍጠር አደጋ በመፍጠር የሚታወቀው በዛብህ ለፋሲል ከነማ ቁልፍ ሰው ሆኖ ቀጥሏል።

👉 ቦታውን እያስከበረ የሚገኘው አበባየሁ ዮሐንስ

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለቡድኑ 10ኛ ጨዋታውን ማድረግ የቻለው አበባየሁ ዮሀንስ በቋሚነት መጫወት እንደሚገባው እያስመሰከረ ይገኛል።

ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን 3-1 በረታበት ጨዋታ ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራትን ኳስ ከማዕዘን ማሻማት የቻለው ተጫዋቹ ሁለተኛዋ ግብ ስትቆጠር የኳሱን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በማድረስ ሂደት እጅግ ቁልፍ የሆነችዋን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማድረስ የተሳካ የጨዋታ ቀንን ማሳለፍ ችሏል።

የተሳኩ ረጃጅም እና አጭር ኳሶችን ማቀበል የሚችለው አማካዩ ከሳጥን ውጪም ኳሶችን አክርሮ ወደ ግብ በመላኩ ረገድም ጥሩ የሚባል አቅም ያለው ሲሆን ለሀዲያ ሆሳዕና አማካይ ክፍል የተለየ አቅምን እየፈጠረ ይገኛል።

በመጀመሪያው ዙር እምብዛም በቋሚነት የመሰለፍ ዕድልን በሆሳዕና መለያ ማግኘት ያልቻለው የቀድሞው የሲዳማ ቡና አማካይ ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ አንስቶ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች በመጀመሪያ ተሰላፊነት እየጀመረ ሲገኝ ከሰሞኑ እያሳየ ከሚገኘው ድንቅ እንቅስቃሴ አንፃር በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የመቀጠሉ ነገር የሚቀር አይደለም።

👉 ያሬድ ባየህ ወደ ተጠባባቂነት መውረድ

የአምና የሊጉ አሸናፊዎች የሆኑት ፋሲል ከነማዎች እርግጥ አሁን ላይ ከመሪው በ10 ነጥብ ርቀው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ቢገኙም የዘንድሮው የቡድኑ እንቅስቃሴ ከአምናው አንፃር እጅግ የተዳከመ ሆኖ ተመልክተናል።

ታድያ በዚህ ሂደት ውስጥ ከሚነሱ መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ አስደንጋጭ የሆነ ግለሰባዊ የአቋም መውረድ ነው። ይህ ጉዳይ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ የሚነሳ ሲሆን በተለይ ግን በመከላከሉ ስፍራ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ላይ ጎልቶ እየተመለከትን እንገኛለን።

ከዚህም መነሻነት ከሰሞኑ ጥሩ ብቃት ላይ ያልነበረው እና ተደጋጋሚ ስህተቶችን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ሲፈፅም የነበረው የቡድኑ አምበል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አርባምንጭ ከተማን ሲገጥም ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወርዶ ተመልክተናል።

በተመሳሳይ ባለፉት ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጣማሪው የነበረው እና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፄዎቹን የተቀላቀለው አስቻለው ታመነም እንዲሁ ለተከታታይ ጨዋታዎች በተጠባባቂ ወንበር ካሳለፈ በኋላ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያሬድ ባየህን ተክቶ ዳግም ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት መመለሱ አይዘነጋም።

ከዚህም ባለፈ ግብ ጠባቂውን ሚኬል ሳማኪን ጨምሮ በቡድኑ መከላከል መስመር ላይ የሚሰለፉት ተጫዋቾች በቀደመው የብቃት ደረጃቸው ላይ አለመገኘታቸው የቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

👉 ብዙ ጥፋቶች የተፈፀሙበት ኤፍሬም አሻሞ

ሀዲያ ሆሳዕና ከሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በድምሩ 46 ጥፋቶች የተፈፀሙበት ጨዋታ ነበር።

በተለይ ሁለቱ ቡድኖች የመሀል ሜዳውን የበላይነት ለመውሰድ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ኃይልን ቀላቅለው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የተመለከትን ሲሆን በዚህ ሂደት የጨዋታው ሂደት በተደጋጋሚ ሲቆራረጥም እንዲሁ አስተውለናል።

ታድያ በጨዋታው በተለያዩ ሚናዎች ሲጫወት የተመለከትነው ኤፍሬም አሻሞ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ጥፋቶች ሲፈፀሙበት ተመልክተናል። በተወሰነ መልኩ ኳስን እግሩ ላይ ለማቆየት ይሞክር የነበረው ኤፍሬም አሻሞ በተደጋጋሚ በሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች የኃይል አጨዋወት ሰለባ ሆኖ ነበር።