የባህር ዳር ከተማው አጥቂ ቅጣት ተላልፎበታል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በባህር ዳሩ አጥቂ ኦሴ ማውሊ ላይ ቅጣት አስተላልፏል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎቹን ከትናንት በስትያ አገባዶ በነገው ዕለት የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎቹን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ያከናውናል። የሊጉ የበላይ አካል የሆነው የአክሲዮን ማኅበሩ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴም በሳምንቱ ተከስተዋል ባላቸው የዲሲፕሊን ህፀፆች ላይ በትናንትናው ዕለት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በትናንት ምሽቱ ዘገባችን መከላከያ ከ ባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ሲለያይ ‘ጨዋታው ሊጠናቀቅ ባለበት ሰዓት (92ኛው ደቂቃ) በቅጣት ምት ምክንያት በቆመበት ወቅት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳይኖር የባህር ዳሩ አጥቂ ኦሴ ማውሊ የተከላካዩ ኢብራሒም ሁሴን የእግር ኳስ ህይወቱን እንዲጨርስ የሚያደርግ ምት በቆመበት ከፍተኛ ሀይል በተቀላቀለበት እግሩ ላይ የመርገጥ ሥራ ሲሰራ የመሐል ዳኛው እና ረዳት ዳኛው በዝምታ ያለፉ ከመሆኑ በተጨማሪ አሁንም በግልፅ በቪዲዮ ምስሉ ላይ እንደታየው ይሄው ተጫዋች ጨዋታው ካለቀ በኋላ የኢብራሒምን አንገት እንዳነቀው ያሳያል’ በሚል መከላከያ አቤቱታ ማቅረቡን ገልፀን ነበር። የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴም ‘ከዳኛ እይታ ውጭ የተጋጣሚ ተጫዋችን ኳስ በሌለበት ሃይል
በተቀላቀለበት የቆመ እግሩን ስለመርገጡና ጨዋታውም ከተጠናቀቀ በኋላ አንገቱን በማነቅ ስለመገፍተሩ በዕለቱ የጨዋታ ታዛቢ ሪፖርት ቀርቦበታል።’ ካለ በኋላ ተጫዋቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 63 በተቁ 1 (ሠ) እና በተቁ 2 መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድ እና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል መወሰኑን አረጋግጠናል።