ዋልያው ከአቋም መፈተሻ ጨዋታ መልስ ልምምዱን ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን በመለየት ልምምዱን ቀጥሏል።

በቀጣዩ ዓመት በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አራት ከማላዊ፣ ግብፅ እና ጊኒ ጋር መደልደሉ ይታወቃል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ከቀናት በፊት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ልምምድ ማሰራት የጀመሩ ሲሆን ከሌሶቶ ጋር ካደረጉት ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች በኋላ ደግሞ ዛሬ ጠዋት የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን በመለየት ከማላዊ እና ግብፅ ጋር ለሚደረጉት ጨዋታዎች ዝግጅታቸውን እንደቀጠሉ ከሰዓታት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ከረፋዱ 4:50 ጀምሮ በተከናወነው የዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር ላይ በትናንትናው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው ዳዋ ሁቴሳ ጡንቻው አካባቢ በደረሰበት መጠነኛ ጉዳት እረፍት ከመሰጠቱ ውጪ 22ቱም ተጫዋቾች ተሳትፈዋል።

በቅድሚያ ተጫዋቾቹ የማፍታታት እና የማሟሟቅ ሥራቸውን ከሰሩ በኋላ በሦስት ቦታ ተከፋፍለው መሐል ባልገባ ይዘት ያለው ልምምድ ሲሰሩ አስተውለናል። በተለያዩ የኳስ ንክኪዎች በተከፋፈለው እና የተጫዋቾችን የኳስ ቅብብል በፍጥነት ለማከናወን ያለመ በሚመስለው መርሐ-ግብር በኋላ ደግሞ በትናንቱ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሙሉ ደቂቃ የመጫወት ዕድል ከተሰጣቸው ጊት ጋትኩት፣ በረከት ደስታ እና ሚሊዮን ሰለሞን እንዲሁም ዘለግ ያለ ደቂቃ ከተጫወቱት ሔኖል አዱኛ፣ በዛብህ መለዮ እና ሽመልስ በቀለ (በኋላ ላይ ከአጋሮቹ ጋር ተቀላቅሎ ጨዋታ አከናውኗል) በስተቀር ሌሎቹ ተጫዋቾች የግማሽ ሜዳ ጨዋታ አከናውነዋል። በዚህ መርሐ-ግብር አሠልጣኝ ውበቱ እና ረዳቶቹ ተከላካዮች እና አጥቂዎች የቦታ እና የሰው አጠባበቃቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉበትን መንገድ እየነገሩ ሲያሰሩ ታዝበናል።

እንደ ከዚህ ቀደሙ ረዘም ያሉ ደቂቃዎች ያልወሰደው እና እምብዛም ከበድ ያሉ ሥራዎች ያልተከናወኑበት ልምምድም ቀትር ስድስት ሰዓት ሲል ተጠናቋል። ብሔራዊ ቡድኑ ነገ እና ከነገ በስትያ በተመሳሳይ ረፋድ ላይ ልምምዱን ከሰራ በኋላ ዓርብ ረፋድ ወደ ማላዊ ርዕሰ መዲና ሊሎንግዌ በማቅናት እሁድ እና ሀሙስ ከማላዊ እንዲሁም ግብፅ ጋር ወሳኞቹን የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች የሚያደርግ ይሆናል።