ከእረፍት መልስ ሊጉ የሚጀመርበት ቀን ተገፍቷል

ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች 25ኛ ሳምንት ላይ የተቋረጠው የሀገራችን ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድር የሚጀመርበት ቀን ይፋ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚከናወነው ውድድር ከ22ኛ ሳምንት ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ሲከናወን ቆይቶ ግንቦት 15 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት እና ጨዋታዎች መቋረጡ ይታወቃል። ቀድሞ ሊጉ ሰኔ 4 ላይ የ26ኛ ሳምንቱን ይቀጥላል ተብሎ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም የብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች ሽግሽግ ስለተደረገባቸው የመጀመሪያው ቀን በሦስት ቀናት ተገፍቷል።

በዚህም ሰኔ 7 4 ሰዓት ሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ በባህር ዳር ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚመለስ አክሲዮን ማኅበሩ ይፋ አድርጓል። ውድድሩም ሰኔ 27 እንደሚጠናቀቅ በመረጃው ተመላክቷል።

በተያያዘ ዜና ውድድሩ ወደ ሌላ ከተማ ይጓዛል የሚለው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህም ከ26ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉት ጨዋታዎች በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።